Monday, August 9, 2010

ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ክፍል 3

ኦ አበዊነ ንቡራዊነ እድ ስዩማን አለ መትልወ ሐዋርያት፡፡
አንቀጽ ተስማሚውን ያወርዳል፡፡ ናፈቅረክሙ ወነአብየክሙ ሲል ነው፡፡ ተውህበ ጳውሎስ ሙቁህ ብሎ ወአካል አንሂ መቁሃን ባለ ጊዜ ተወህቡ፡፡ አገብአ ለኤልዛቤል ወስተ ምስካባ ዘቀዳሚ ወእለሂ ዘመው ምሳሌሀ ባለ ጊዜ አገብጾሙ፡፡ ትህምክህሙ ቤተ ክርስቲያን አንተ ውስተ ባቢሎን ዘግብጽ ብሎ ወማርቆስ ባለ ጊዜ ይኤምኃ ክሙ እንዳለበት፡፡ ከሃዋርያት ቀጥላችሁ ሃዋርያትን መስላችሁ በአንብሮተ እድ የምትሾሙ አባቶቻችን እናከብራቸዋለን እናገኛቸዋለን፡፡ ከሊቀ ጳጳስ ጀምሮ እስከ ቄስ ያሉት በአንብሮተ እድ ይሾማሉ፡፡ ቅብዓት ያለበት ነው ዲያቆን በአንብሮተ እድ ይሾማል ቅብአት የለውም ከዚያ በታች ያሉትን በቃል ይሾሟቸዋል፡፡
እስመ ነሳእናከሙ አስተብቋዕያነ ለነ ለኀበ እግዚአብሔር፡፡

ወደ እግዚአብሔር ልታማልዱን፡፡ አስተበቁዐነ፤ እግዚአብሔር አግኝተን ተቀብለናችኋልና እናከብራችኋለን እናገናችኋለን ሃተታ፡- ሊቀ ጳጳሱ በሞተ ጊዜ የበቁትን ደጋጎቹን መርጠው ስማቸውን በቅፋፍ ጽፈው ያለፈው ኦ እግዞኦ አዕርፍ ነፍሰ አቡነ እገሌ ለሚመጣው ኦ እግዚኦ አንብር ለነ ዲበ መንበሩ ኖላዌ ሄረ ኢንኩን ከመ መር ኤት ዘአልቦ ኖላዊ ወኢይምስጠነ ተኩላ መሳጢ እያሉ ይፀልዩበታል፡፡ ፀሎታቸውን ሲፈጽሙ አንድ ብላቴ አምጥተው እያነሳህ ስጠን ይሉታል እያነሳ ይሰጣቸዋል ሳያይ መልሰው ይቀላቅሉታል አንዱን 3 ጊዜ መላልሶ ይሰጣቸው እንደሆነ ያሮስ ያሮስ አኪዮስ አኪዮስ ብለው ይሾሙታል ይደልዎ ይደልዎ ማለት ነው አንዱን 1 ጊዜ አንዱን 1 ጊዜ የሰጣቸው እንደሆነ ግን ከጸሎቱ ይጨምሩበታል ከሐዋርያት ሲያያዝ የመጣ እንደሆነ ይሁዳ በወጣ ጊዜ በይሁዳ እግር እኛ ባወቅን ማትያስ እና ባርናባስን መርጠናል አንተ እገግዚኦ ማእምረ ኩሉ ልብ አርኢ 1ደ እምአሉ ዘኃረይከ ዘይነስአ ለመልእክተ ሲመት ዘሐዋርያት፡፡ ኩላሊት ያመላለሰውን ልቡና ያሰበውን መርምረህ የምታውቅ አቤቱ ይህችን ሐዋርያተን ሹመት ገንዘብ የሚያደርጋትን ከነዚህ ከሁለቱ የመረጥከው አንዱን ግለጥልን ብለው፡፡ በአስተ አጸውዎሙ ይላል፡፡ እጻ አጣጣላቸው ወወዕአ ላእለ ማትያስ ይላል እጣ በማትያስ ወጣ መከራ የሚቀበልበት ነውና በዓለ፡፡ አንድም ለማትያስ ዋጋ የሚያገኝበት ነውና ለ አለ ወተኁለቁ ምስለ 0 ወ 1 ሐዋርያት ከ01 ሐዋርያት 02ኛ ሁኖ ተቆጥሯልና እንዲህ አለ፡፡
ወነሳእሙ በመዋእሊነ አስተሳሰብ ቋዕያነ ለነ ለህበ እግዚአብሔር እሎንተ 2 ኤተ ሊቀነ ጳጳሳት፡፡


የእስክንድርያ ሊቃነ ጳጳሳ እለ እስክድርስና አትናቴዎስን ወደ እግዚአብሔር ሊያማልዱን ተቀብለናአዋልና አስተበቁዐነ ይላል፡፡ እግዚአብሔር አግኝተን ተቀብለናቸዋልና እናገኛቸዋለን እናከብራቸዋለን ሃተታ፡- ዕለ እስክንድሮስ አርዮስን ተከራክሮ ረትቷልና አትናትዮስም በእሱ ሃዘን በርሱ ፀሎት በዘመኑ አርዮስ ሙቶዋልና፡፡
ብጹእ ጳጳስ አባ እገሌ ዘሀገር እስክንድርያ አባይ እስክንድርያ፡፡ በእስክንድርያ በመዲናይቱ ሀገር የተሸመ አባ እገሌን፡፡
ወዲበ ርእሰ ሃገረ አበዊነ ብጹእ ከጳጳስ በመዲናይቱ በአክሱም የተሸመ ንዑድ ክቡር የሚሆን አባ ሰላማን እንወደዋለን እናከብረዋለን እንዳለፈው ተርክ፡፡
አንድም አሎንተ ክልኤተ ሊቃነ ጳጳሳተ አባ እገበሌ ዘሀገር አባይ እለ እስክንድርያ ወዲበ ርእሰ ሀገረ አበዊነ ብፁእ ጳጳስ አባ ባስሊዎእ፡፡
የእስክንድርያውያን አባ እገሌ የሀገራችን ጳጳስ አባ ባስልዮስን እናከብራቸዋለን እነወዳቸዋለን እንክንድራውያንስ ሊቀጳጳስ ይሁን የሀገራችን እለምን ሊቀጳጳስ አለው ቢሉ እስክንድሪያው ሊቀ ጳጳስ አስጠግተ ስምኦንን ከሌዊ አስጠግቶ ካህናትን ህሉፋነ ፍኖት ከበቱ ፍኖተ እግዚኦሙ እንዳለ አንድም ከሊቀ ጳጳስ ማዕርግ አድርሶ የሚሰደው እለሆነ በመንበሩ አስቀምጦ ጭራውን መቋሚያውን መስቀሉን ሰጥቶ የሚሰደው ሰለሆነ አንድም ስም ሰጥተው ግብር ነስተውታል ወያክብርዎ በስመ ሊቀናት በህቲቱ ዘንበለ ይኩን ሎሩ ስልጣነ ዝንቱ እንዲል በእእክንድር እስክንድርያ ተብላለች፡፡ ታሪክ እስክንድር የሚባል ገናና ንጉስ ነበረ ስነ ባዓል ለማየት መንግስት ለማድረስም ቢሊ ለሌላም ነበር ቢሉ አንድም ያቁመን ለመተጋት እየሩሳሌም ወጣ ከወጣ ዘንድ ሲመለስ ሰም የሚያስጠራ ልጅ የለኝ ምን ሰርቼ ስሜን ላስጠራ አለ ድልድይ ሰርተህ አስጠራ አሉት ይህች እስክድርያ ማይ ጽንፋ ማይ ሃጹራ ይላታል ውሃውን በመዘውር በልሶ የብረት አምድ እያቆመ የብረት ድልድይ እየደለደለ በኖራ እየገለበጠ በብረት እየጠረቀ የብረት ሰረገላ እያሸጋገረ የብረት መረባ ሰርቷል፡፡

ልማደ ሰብእ ልማደ እንስሳ የሚወርድበት እንደ መሽረብ ያለ ሰርቶ አዞ ጉማሬ እየወጣ እንዳያውክ ገባሬ ተአምር አመጽ ኤልሳእን ቀብሮበታል በዚያ ላይ ሶስት ድስት ሙሉ ቀብሮበት ሂዷል፤ ይህ የተደረገ በዘመነ ቡሉይ ነው ሲያያዝ ከዘመነ ሀዲስ ደርሷል ከዘመነ ሀዲስ እስከ ዘመነ ሊቃውንት ደረሰ አትናቴዎስ በእስክንድርያ ተሹሞ ሳለ በዘመኑ ረሀብ ሆነ፤ ወርቅ ተቀብሮ እያለ ነደያን እየተራቡ እመከመ ረከብኩ ሞገሰ መቅድመ አምላክየ እየሀድጎ ለዝንቱ አድራማሌቅ ሙክራበ ሰገል እያለ ሲጸልይ ተምኔቱ ሳይፈጸምለት ሞተ፡፡ ከሱ ቀጥሎ ቴዎፍሎስ ተሸመ እሱም በዘመኑ ረሀብ ሆነ ወለእመ ለከብኩ ሞገሰ በቅድመ አምላክየ እየሀድጎ ለዝንቱ አድራማሌቅ ምኩራበ ወገል እያለ ሲያዝን ይኖር ነበረ ኃላ ግን አልአርታ የምትባል የሮም ንግስት ብዙ ሰራዊት አስከትላ ሄደች ስለምን ቢሉ ለምናኔ ብዙ ሰው አስከትሎስ ምናኔ የለም ብዙ ገዳማተ ግብጽን እጅ ለመንሳት በገዳማተ ግብጽ ካቱ አበው ለመባረክ ከአበው አንዱ እሱ ነውና ወደ እሱ ሄደች አዝኖ አየችው ምነው አዝናሀል አለችው እኔ አላዝን ማን ይዘን ወርቅ ተቀብሮ እያለ ነደያን እየተራቡ አላት አታስኮሰትረውምን አለችው ባይቻለኝ ባንተ ጸሎት በእግዚአብሔር ረድኤት አስኮሰትርልሀለሁ ብላ ብታስኮሰትርለት ቴዳ ቴዳ የሚል ሶስት ድስት ሙሉ ወርቅ ተገኝቷል ቴዳ ማለት ታኦስ ማለት ነው ታኦስ የጌታ ስም የጌታ ለነደያን ይገባል ብሎ አንዱን ለነድያን መጽውቶሎታል አንዱን ቴዳ ማለት ቴዎዶስዮስ ማለት ነው ብሎ ለንጉሱ ሰዶለታል፡፡ ንጉሱም ለበረከት ያህል ከፍሎ አስቀርቶ መልሶ ሰዶለታል፡፡ በዚህ አብያተ ክርስቲያናትም ይነጽት ለነዳያንም ይመጸውተው አልታወቀም፡፡ አንዱን ቴዳ ማለት ቴዎፍሎስ ማለት ነው ይሄ የእኔ ገንዘብ ነው ብሎ በዚህ ሰባት ያህል አብያተ ክርስቲያናት አንጾበታል፡፡ ታቦተ እየሱስ ታቦተ ማርያም ታቦተ ሚካኤል ታቦተ ሩፋኤል በዘባነ አንበሪ የታነጸ በዚያ ጊዜ ነው ታቦተ ኤልሳእ ታቦተ ዮሐንስ መጥምቅ ይህ አንድ ወገን ነው፡፡

ታቦተ ኤልሳቤጥ ታቦተ መርቆሬዎስ ነው ወረቅ ስለተገኘባተ አባይ አላት ይሕስ አባ ሕርያቆስ የሚሻ መንፈሳዊ የስጋው የደሙን ነገር ነው የመንፈሳዊ የስጋው ደሙን ነገር ሲናገር መጥቶ ማሩን አምርሮ ወተቱን አጥቁሮ ወርቅ ተገኘባት ብሎ አባይ አይላትም ብሎ ወትከውን አሃቲ ሀገር ምስዋኦ ለእግዚአብሔር እንዲል በአራቱ ማዕዘን ሐይማኖት ሲጠፋ እሰከ ዕለተ ምፅሐት ወልድ ዋህድ ስትል ትኖራለችና ርእሰ አክሱም ሀገር መላ ኢትዮጵያ፡፡
01 ይ ዲ በእንተ ብፅእት፡፡
ወብጽእት አንቲ እንተ ተአምኒ ከመ ይከውን ቃል ዘነገሩኪ ተብላ በኤላሳቤት ቃል ስለተመሰገነች፡፡
ወፍስሕት፡፡
ተፈስሂ ተፈስሂ ተብላ በመልአኩ በገብርኤል ቃል ስለተበሰገነች ወስብሀት ለኩሉ፡፡
ክብር በውስተ ነብያ ክቡር በውስተ ሊቃውንት እንዲል በሁሉ ዘንድ ስለተመሰገነች ወቡሩክት፡፡
ቡሩክት እንቲ እምአንስት ተብላ ስለተመሰገነች፡፡
ወቅድስት ወንጽህት እግዝእትነ ወላዲተ አምላክ ማርያም ድንግል ንጽህት ኩሉ ጊዜ ተብላ ስለ ተመሰገነች አምላክን ስለወለደች ስለ እመቤታችን ብለህ አንድም እሷን አማለጅ በማድረግ እጣን ቋጥረው ግብር ሰፍረው መባዕ ይዘው ወደ ቤተ እግዚአብሔር የሚሄዱት አስባቸው ይበል፤ እግዝእትነ እለ ከግብርናተ ዲያቢሎስ ነጻ አውጥቶ የሚገዛን ከእሷ በነሳው ስጋ ስለሆነ ነው፡፡
02 ወበእንተ ቅዱሳን ክቡራን፡፡ ጽኑዓን ክቡራን፡፡
መንፈሳውያን፡፡ ረቂቃን ስለሚሆኑ፡፡ ሊቃነ መላእክት፡፡
መዐርጋቸውን መናገር ነው፡፡ ሰማያውያን፡፡
ቦታቸውን መናገር ነው፡፡
ወኃያላን፡፡
ኃያላን ስለሚሆኑ ስለዚህ ብለህ አንድም በእነዚህ አማላጅነት፡፡ ሀተታ፡- በተፈጥሮ ኃይል ይሰጣቸዋልና አንድም በቅዳሴ በተራድኦ ምክንያት ይጨመርላቸዋልና፡፡
ሰባኪ፡፡
ነስሁ እስመ ቀረበት ምነግስተ ሰማያት እያለ፡፡
ወጸያሄ ፍኖት ዮሐንስ መጥምቅ፡፡ ጺሁአ ጸፍቶ እግዚአብሔር እያለ ስለሚያስተምር መጥምቀ መለኮት ስለሚሆን ስለዮሐንስ ብለህ አንድም በእሱ አማላጅነት፡፡
ወበእንተ ቅድሳን ስቡሃን ወላእካን ማትዮስ ወማርቆስ ሉቃስ ወዮሐንስ 4ቱ ወንጌላውያን፡፡
ንጹሀን ክቡራን ላእካነ ቃል ስለሚሆኑ ስለ 4ቱ ወንጌላውያን ስለ ማቴዎስ ስለ ማርቆስ ስለ ሉቃስ ስለ ዮሐንስ ብለህ አንድም በዚህ አማላጅነት ማቴዎስና ዮሐንስ ከቦታቸው ይተረጎማሉ፡፡
ማርቆስ ማለት አንበሳ ማለት ነው አንበሳ ለላህም ጌታው ነው ይሰብረዋል፡፡ እሱም ከግብጽ ላምህን አጥፍቷልና አንድም ንህብ ማለት ነው ንብ የማይቀስመው አበባ የለም፤ እሱም አስቀድሞ ከጌታ ኋላ ከኃዋርያት ተምሯልና አንድም ካህን ማለት ነው ወአምጽኡ ማረዜድዮስ እንዲል፡፡
ሉቃስ ማለት መስበር ማለት ነው ብስራት ማለት ነው ብስራት መልአክን ይጽፋልና አንድም ተንሳኢ ማልት ነው ለስብከተ ውንጌል ይጠናልና አንድም አቃቤ ስራይ ማለት ነው፡፡ ዘስጋ ነበረ ኃላ ግን አቃቤ ስራይ ዘነፍ ሁኗልና፡፡
03 በእንተ ቅዱሳን አግብርቲከ ክቡራን ባለሟሎችህ ስለሚሆኑ ሀተታ፡- የባለሟልነት ስማቸው ነው ዳዊት ገብርየ ሙሴ ገብርየ እንዲል፡፡
ጴጥሮስ
ጴጥሮስ ማለት መሰረት መሰረትነቱ የሀይማኖት የልጅነት ነው፡፡ ወያእቆብ ስለያዕቆብ ብለህ ያዕቆብ ማለት አእቃጼ ሰኮና አሃዜ ሰኮና ማለት ነው የቀደመው የዕቆብ ሰኮና ኤሳውን ይዞ እንደተወለደ እሱም ወንጌል ሲያስተምር በዚያው ይሞታልና አእቃጼ ሰኮና ኤሳው እንደሆነ በትምህርቱ የመናፍቃንን ትምህርት ያሰናክላልና፡፡
ወዮሐንስ
ስለ ዮሐንስ ብለህ ዮሐንስ ፍስሐ ወሐሴት ርህራሄ ወሳህል ማለት ነው ፍስሃ ወሀሴት አለ ቅብአ ትፍስህት መንፈስ ቅዱስ ያስጣልና ርህራሄ ወሳህል አለ በጸጋ ዘነሳእክሙ መጸጋ ሀቡህ በእንቱ ዘነሳእክሙ በከንቱ ሀቡ ባለው ጸንቶ ያስተምራልና፡፡
ወእንድርያስ
ስለ አንድርያስ ብለህ አንድርያስ ማለት ተባእለ ለመስቀል በኩረ ሐዋርያተ ማለት ነው ተባእ ለመስቀል አለ እስከ ሀገር በላእተ ሰብእ ሄዶ አስተምሯልና፡፡
ፊሊጶስ
ፊሊጶስ ማለት ምፍቀሬ አኅው ማለት ነው ፊልሳዳፎስ እንዲል አንድም አሃዜ ኪናት ረያጺ አፍራስ ማለት ነው አንድም ስውር ቦታ ማለት ነው ፌላሌምሎሞንም ንዑ ንህድር ብሔር ፊልሞን እንዲል፡፡
በርተለምዮስ
ስለ በርተለምዮስ ብለህ በርተለምዮስ ማለት ተክል የማጠጣት ግብር ያለው ልጅ ማለት ነው፡፡ ኩን ወልደ ኃይል ኩን ወልደ የማን እንዲል፡፡ አንድም ዕለቱን ወይን ተክሎ ለመስዋእት አድርሷልና፡፡
ቶማስ
ስለ ቶማስ ብለህ ቶማስ በለት ፀሀይ ማለት ነው ሁለቱ አስማቲሁ ለፀሀይ 1ዱ ኦርያሬስ ወካልኡ ቶማስስ እንዲል፡፡ ወማቴዎስ
ስለ ማቴዎስ ብለህ ማቶዎስ ማለት ህሩይ እመጸብሀን ማለት ነው ግብር የሚያስገብርበት መርጦታልና፡፡
ወያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ
ስለ ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ ብለህ ወልደ እልፍዮስ ማለት ተለይቷል አንጂ ትርጓሜው እንዳለፈው ነው፡፡
ታድዮስ
ስለ ታድዮስ ብለህ ታድዮስ ማለት ዘርእ ወማእረር ማለት ነው ኦርቲን እንደዘር ወንጌልን እንደማእረር አድርጎ አስተምሯልና አንድም ዕለቱን ሰንዴ ዘርቶ ዕለቱን ለመስቀእት አድርሷልና፡፡
ወስምኦን ወማትያን
ሰለ ስምኦንና ሰለማትያን ብለህ ማትያን ማለት ምትክ ማለት ነው ማትያስ ማለት ፀሐይ ማለት ነው፡፡
0ቱ ወ2ቱ ሐዋርያት፡፡
ስለ አስራ ሁለቱ ሐዋርያት ብለህ አንድም በእነዚህ አማላጅነት አስባቸው ስማቸውን አስቀድሞ ቁጥራችን ወደኋላ አመጣ
ወያዕቆብ ሐዋርያ እኁሁ ለእግዚእነ ኤጰስ ቆጰስ ዘኢየሩሳሌም፡፡ በኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስነት ስለተሸመ የጌታችን ወንደም ስለሚሆን ስለ ወንጌል ዙሮ ስለእስተማሩ ስለያእቆብ ወንጌልን ዙሮ ስለ አስተማሩ ያዕቆብ ብለህ አንድም በእሱ አማለጅነት ሀተታ መገናኛው ጉንዱ አልኣር ነውአልአዛር ቅስራንና ማትያንን ይወልዳል ቅስራ እያቄም እመቤታቸንን ጌታን ማትያን ያዕቆብ ዮሴፍን ዮሴፍ ያዕቆብን ይወልዳል፡፡ በአንፃር ያለ ነውና እኁሁ አለ፡፡
ለተዘምዶ እነ ያዕቆብ እነ ዮሐንስ ወለደ ዘብድዮስ ይቀርቡታል ብሎ እናቱ በህጻንነቱ ሙታ ከአባቱ ቤት አግኝታው ከጌታ ጋር እያጠባች አሳድጋዋለችና ኃሊብ ድንግልናዊንስ እሩቅ ብእሲ መጥባት አይቻለውም ብሎ እንደ እናት ሁና ኣድጋዋለችና ኤጲስ ቆጰስ ዘእየረሳሌም አለ ያዕቆብ መኮነ እግሩ ከመ እግረ ነጌ ይላል ከገድል ጽናት የተነሳ እግሩ እንደሙቀጫ ተድበልብሎ ነበር እና ለስበከተ ወንጌል አይፋጠንም ብለው በኢየሩሳሌም ሹመውት ሄደዋል፡፡ ከሀዋርያት አንድ አንድ ደዌ የሌለበት አለ ቅዱስ ጴጥሮስንም ወኮነ ድውየ ወድግዱገ ስጋ ይለዋል አጸናበትም አንጂ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ቀጭን ሰጥር ውጋት አዳጊት የምትባል ራስ ፍልጠት ደዌ ነበረበት በእዚያውስ ላይ ሐዋርያ ደመና ጠቅሶ ካሰበው ደርሶ ብዙ አስተምሮ አሳምኖ ብዙ አጥምቆ ይውል የለምን ቢሉ በኢየረሳሌም የነበሩ አይሁድ ምሁራነ ምፃሕፍተ ነቢያት ናቸው ከእርሱ በቀር የሚያውቅባቸው የለም ብለው ሹመውታል ያገሩን ሰርዶ ባገረ በሬ እንዲሉ፡፡ ሐዋርያ አለው ወንጌል ዙሮ አስተምሯልና
ወቅዱስ ወስቡህ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት ወቀዳሜ ሰማእት፡፡
ንጹህ ክቡር ሊቀ ዲያቆናት የሰማዕታት ደገኛ አንድም የሰማእታት ፊታውራሪያቸው ስለሚሆን ስለ እስጢፋኖስ ብለህ አንድም በእሱ አማላጅነት እስጢፋኖስ ማለት ወደብ መደብ ለሆቴ ደንጊያ ማኅቶተ ቁድ ማለት ነው ንፋስ የማያስገባ ብርሃን የማይከለክል ፋና ነው ቀዳሜ ሰማዕት አለ ከጌታ ቀጥሎ ከሐዋርያት አስቀድሞ መከራተ የተቀበለ እሱ ነውና 6ቱን ዲያቆናት መርጠው 7ኛ እርሱን መደበኛ አድርገው ሹመውታልና ሊቀ ዲያቆናት አለ፡፡
04 ወኩሎሙ ቅዱሳን ወሰማእት እለ እረፉ በርትእት ሐይማኖት፡፡
ውሎ ውሎ ከቤት ኑሮ ኑሮ ከመሬ እንዲሉ ኃይማኖታችንን አንክድም ብለው ስለሞቱ ሰማእታት ብለህ አንድም በነዚህ አማላጅነት፡፡
ጳውሎስ
ስለ ጳውሎስ ብለህ አንድም በእሱ አማላጅነት ጳውሎስ ማለት ነዋየ ህሩይ ማለት ነው፡፡
ጤሞቲዎስ
ስለ ጤሞትዮስ ብለህ ጤሞትዎስ ማለት ዘአልቦቱ ጥሬት ማለት ነው፡፡
ሲላስ
ስለ ሲላስ ብለህ ሲላስ መለት ፀሐይ መለት ነው፡፡
ወበርናባስ
ስለ በርናባስ ብለህ በርናባስ ማለት ወልደ ፍስሀ ማለት ነው፡፡
ቲቶ
ስለ ቲቶ ብለህ ቲቶ መለት አርቅ ማለት ነው፡፡
ወፍልሞና
ስለ ፍልሞና ብለህ ፍልሞና ማለት ስውር ቦታ ማለት ነው፡፡
ወቀሌምንጦስ
ስለ ቀሌምንጦስ ብለህ ቀሌምንጦስ ማለት ግንብ ማለት ነው፡፡
፸ወ2ቱ አርድዕት
ነሣሣለትና ስለ ሰባሁለቱ አርድዕት ብለህ አንድም በእነዚህ አማላጅነት አስባቸው፡፡
5ቱ ፻ት ቢጽ፡፡
ስለ አምስት መቶ ቢጽ ብለህ አንድም አንዚህ አመላጅነት በማድረግ ሀተታ፡- እሊህ ከ5፻ ብቅ 6፻ ዝቅ እንደሚሉ በዕለ አርብ እንደ አሸን ፈልተው ከእግረ መስቀል የተነሱ ናቸው ቢጽ አላቸው በተፈጥሮ ከእሊህ እስከ እርገት እስከ ጰራቅሊጦስ ያስተማረ አለ ወዲያው እስከ ትንሳኤ ቆይቶ ያረፈ አለ፡፡
3፻0ወ8 ርቱዓነ ሀይማኖት፡፡
ሃማኖታቸው ስለ ቀና ስለ ሶስት መቶ አስራ ስምንቱ ሊቀውንት ብለህ አንድም እነዚህን አማለጅ በማድረግ እጣን ቋጥረው ግብር ሰፍረው መብዓ ይዘው ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱትን አስባቸው አንድም እንዚህ አማላጅ ስለአደረጉ፡፡ አንድም በእነዚህ አማላጅነት አስባቸው፡፡
05 ለእሉኒ ወለኩሎሙ ተዘከሮሙ ለከ እግዚኦ፡፡ ያለፈውን የሚያጣራውን ላንተ ማደሪያ ቤተሰብ ወገን ለሚሆኑ አቤቱ አስባቸው፡፡
ለብጹእ ወለቅዱስ ሊቃነ ጳጳስ አባ እገሌ ንዑድ ክቡር የሚሆን አባ እገሌን፡፡
ወብዑእ ወቅዱስ አባ እገሌን፡፡ ንዑድ ክቡር የሚሆን አባ እገሌን አስባቸው አንድም ለእነዚህ ብለው እጣን ቋጥረው ግብር ሰፍረው መብዐ ይዘው ወደ ቤተ እግዚአብሔር የሚሄዱትን አስባቸው፡፡
06 ከመ ትዕቀቦሙ በሕይወቶሙ በሕይወተ ስጋ ሳሉ ከመከራ ስጋ ትጠብቃቸው ዘንድ አንድም ማሰብ ሌላን ዓለም ጠብቃቸው፡፡
ወታድኅኖሙ፡፡
ታድናቸው ዘንድ፡፡ አንድም ማዳን ሌላን አለ አድናቸው፡፡
ወትሥረይሎሙ አጢአቶሙ፡፡
አጢአታቸው ታስተሰርይላቸው ዘንድ አንድም ማዳን ሌላን አለ ኃጢያታቸው የሚያስተርይላቸው
ወትምሀረነ ኪያነ ሂ በጸሎተ እግዚእሆሙ ለዓለን ዓለም፡፡
ትምሀረነ ካለ ለነሂ ኪያነ ካለ ትምሀር ባለ በቀና ነበረ ነገር ግን ልማደ መጽሀፍ ነው እኛንም በእሳቸው ጸሎት ይቅር ትለን ዘንድ አንድም ማሰብ መጠበቅ ማዳን ኃጢያትን ማስተሰረይ ሌላን አለ በሳቸው ጸሎት ለዘለዓለሙ ይቅር ይበለን፡፡
ይቆየን .........

ውዳሴ ማርያም አንድምታ የሰኞ ክፍል 1

ይኸነን መጽሐፍ ኤፍሬም ሶርያዊ ኤፍሬም ለብሐዊ ተናግሮታል፡፡ ሶርያዊ በሀገሩ ለብሐዊ በተግባ ያስኛል፡፡ ይህም ቅዱስ ኤፍሬም የያዕቆብ ዘንጽቢን ደቀ መዝሙር ነው፡፡ ያዕቆብ ዘንጽቢንም ቁጥሩ ከሰለስቱ ምዕት ነው፣ ለአውግዞተ አውአርዮስ ሲሄድ አስከትሎ ሂዶ ነበር፡፡ አርዮስ አውግዘው ሀይማኖት መልሰው ተመልሰው ካደሩበት ቦታ አምደ ብርሃን ከምድር እስከ ሰማይ ተተክሎ ለሊቱን በህልሙ ራዕይ ያያል፡፡ ራዕዩም እንደገለጽክልኝ ባለበኔቱንም ግለፅልኝ ብሎ ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክት የታዘዘ መልአክ መጥቶ ባስልዮስ ዘቂሣርያ ነው፡፡ለቤተ ክርስቲያን አምድ ፅንዕ ነውና በትምህርቱ የሰውን ልቦና ብሩህ ያደርጋልና እንዲህ ባለ አርአያ አየኸው አለው፡፡ ባስልዮስም ቁጥሩ ከሰለስቱ ምእት ነው ደረሶም ተመልሶም እንደ ሆነ በደዌም በዕርግናም ምክንያት ቀርቶ እንደሆነ የቀረበት ምክንያት ከዚህ በኃላ መምህርን ካወጡበት ሳያገቡ ትቶ መሄድ ፈሊጥ አይደለምና መምህን ካወጣበት አግብቶ ሰለሦስተ ነገር ይሄዳል መጀመሪያ እንዲህ ካለ ሰው ጋራ ቢጫወቱ መንፈሳዊ ነገር ይገኛልና ብሎ ሁለተኛ በጆሮ የሰሙትን በዐይን ቢያዩት ይረዳልና ብሎ ሦስተኛ የመንፈስ ቅዱስን ነውን ወይስ ሰይጣን ተጫውቶብኝ ይሆን ብሎ ስለ ሄደ ግን እንዳየው ሆኖ አላገኘውም በወርቅ ወንበር ተቀምጦ በወርቅ አትራኖስ የወርቅ ወንጌል አቀርግቶ ካባ ላንቃ ለብሶ ኪፋር ጠምጥሞ መነነሳንሱን ቢያዩት የሐር መያዣውን በያዩት የወርቅ መነሳንስ ይዞ ሲያስተምር አግኝታል፡፡ ወተሐዘቦ ልቡ ለኤፍሬም ከመ ሥጋዊ ውእቱ እንዲል፡፡
እስመ ሚስጥራትን ይትከሠታ ለትሑታ እስመ ውስተ ምይንት ነፍስ ኢተኀድር ጥበብ አንዲል፡፡ ወይሬእዩ ርእሶሙ ከመ መነፈስ እንተ ህልፈት ይላል ለመንፈስ ቅዱ ሁለት ግብ አለውን ወይስ ሰይጣን ተጫውቶብኝ ይሆን እያለ ሲያወጣ ሲያወርድ ዐራት ነገር አይቶ ይረዳል፡፡ መጀመሪያ ካፋ ነጸብራቅ እሳት እየወጣ ሕዝቡንም ሲዋሃዳቸው ያያል ይህም ትምህርቱ ነው፡፡ ሁለተኛ እርብ መጥታ በራሱ ላይ ስታርፍበት ሦስተኛ ተሐዋስያን ከልብሱ ላይ እያረፋ እንደቆሎ ሲረግፍ ያያል፡፡ ይህን መናፍቃን ፍጡር ፈጣሪ ይመስላ ያቃጥላልን ብለው እንቃወማለን ይላሉ አይፈርስም ለከዊነ እሳት ደርሶ ነበርና ያቃጥላል ዐራተኛ ስሙን ያያውቅ ሀገሩን ያይጠይቅ ኤፍሬም ሶርያዊ ኤፍሬም ለብሐዊ ብላችሁ ጥሩልኝ ከማእዘነ ቤተ ክርስቲያን ባንዱ ቆሞ ይጸልይላችኋል ብሎ አስጠርቶ በአስተርጓሚ ሲጫወቱ ጨዋታው ባይከተትለት አባቴ ጸልይና ያንተ ቋንቋ ለእኔ ይገለጥልኝ፡፡

ጸልዮ የባስልዮስ ቋንቋ ቅርዕ ነው ለኤፍሬም የኤፍሬም ቋንቋ ሱርስት ነው ለባስልዮስ ለገልጾላቸው ሲጨዋወቱ አድረው ሲነጋ አሰናብተኝ ሊሂድ አለው፡፡ መች ልትሄድ አምጥሃላ ልትኖር ነው እንጂ ብሎ ሕዝባዊ ነው ቢሉ ዲቁና ዲያቆን ነው ቢሉ ቅስና ሽሞ ከሀገረ ስብከቱ ሀገር ከፍሎ አስተምር ብሎ ሰጠው፡፡ በሰልዮስም ይህን መልበሱ ስለ ክብረ ወንጌል ነው፤ ዛሬ ካህናት አክሊል ደፍተው ኩፋር ጠምጥመው ካባ ላንቃ ለብሰው ስጋውን ደሙን እንዲያከብሩ እንዲለውጡ እርሱስ በውስጥ የሚለብሰው ማቅ ነበር፡፡ ከዚህ በኃላ እም አዝማደ ነገስታት ይላታል ከአዋልደ ነገስታት ወገን የምትሆን አንዲት ሴት ነበረች ኃጢያቷን እየፃፈች የምታኖር፡፡ ስለምን ቢሉ ለመንገር ብታፍር፡፡ አንድም ቢበዛ፡፡ አንድ ቀን መጥታ እንደተጠቀለለ ይዛ አባቴ በዚህ ያለው ይፋቅልሽ በለኝ አለችው፡፡ ይፋቅልሽ አላት ገልጣ ብታይ አንዲት ቀርታ አየች ዘዕጽብ ለነጊር ለገቢርም ይላታል ይህችሳ አለችው ይህስ ለቅዱስ ኤፍሬም ቢቻል እንጂ ለእኔ አይቻለኝም አላት፡፡ አሁን ለእርሱ የማቻለው ሆኖ አደለም ቅዱሳን የራሳቸው ክብር ኪገለጥ የወንድማቸው ክብር ቢገለጥ ይወዳሉና፡፡ ዳግመኛም ስጥመጣ ስትሄድ ድካም ያለባት ነውና ቀኖና ይሁናት ብሎ ነው ሄዳ አባቴ በዚህ ያለው ኃጥያትሽ ይፋቅልሽ በለኝ አለችው

ይህስ ለሊቀ ጳጳሱ ለቅዱስ ባሰልዮስ ቢቻለው እንጂ ለእኔ አይቻለኝም አላት አሁን በእርሱ የማይቻለው ሆኖ አይደለም፡፡ ቅዱሳን የራሳቸው ክብር ኪገለጥ የወንደማቸው ክብር ቢገለጥ ይወዳሉና፡፡ ዳግመኛም ስትሔድ ስትመጣ ድካም ያለባት ነውና ቀኖና ይሁናት ብሎ፡፡ ስለሄድሽ ግን እንደቀደመው በህይወተ ስጋ አታገኝውም ሙቶ ሊቀብሩት ይዘውት ሲሄዱ ታገኝያለሽ ሳትጠራጠሪ ከአስክሬኑ ላይ ጣይው ይፋቅልሻል፡፡ ብትሄድ ሙቶ ሊቀብሩት የዘውት ሲሄዱ አገኘች አትጠራጠር ካስከሬኑ ላይ ብትጥለው ተፍቆላታል ይህም የካህናትን ማዕርግ ደግነት ይጠይቃል፡፡ በህይወተ ስጋ ሳሉ ከሞቱም በኃላ አጢያት እንዲያስተሰርዮ ስምኦን ዘአምድ የያዕቆብ ዘንጽቢን ደቀ መዝሙር ነው አብሮት ተምሯል ሊጠይቀው መጣ ሰላም ለኪ ኦ እግዝእትየ ቅድስት ድንግል እያለ ሲያስተምር ሰማሁ፡፡ ኦ እግዝእትየ ከማን አገኘኸው መምህራችን አልነገረን አለው፡፡ ነግሮናል እንጂ አልነገረንም ይመስክር ተባብለው ከመቃብሩ ላይ ቢሄዱ አስሩ ጣቶቹ እንደ ፋና እያበሩ ተነስቶ በህይወትየ እብለኪ ሰላም ለኪ ኦ ቅድስት ድንግል ከመ ስምኦን ዘአምድ፡፡ ወድህረ ሞት የሰ ኩሎሙ አዕፅምትየ ይብሉኪ ወይወድሱኪ ሰላም ለኪ ኦ እግዝእትየ ድንግል ከመ ኤፍሬም ሶርያዊ ብሎ መስክሮለታል፡፡

ይህም የቅዱስ ኤፍሬም ጸጋው ክብሩ ነው፡፡ ከሞተ በኋላ የሚናገረውን አውቆ ለማመስገን ሶርያዊ በሀገሩ ያሰኘው እስከዚህ ነው፡፡ ለብሐዊ በተግባሩ ቢረሌ በርጠብ ብርጭዎ ኩዝ ካቦ እየሰራ የዐመት ልብሱን የዕለት ምግቡን እያስቀረ ይመፀውት ነበር ሲመፀውትም መስላሴ በመላእክት በፃድቃን በሰማዕታት ስም አይመፀውትም በእመቤታችን ስም ይመፀውት ነበር ንቋቸውን አጥቅቷቸውን ነውን ሰለምነው ቢሎ ንቋቸም አጥቅ ቷቸውም አይደለም የእመቤታችን ፍቅር ባያደርሰው ነው፡፡ እመቤታችንን ከመውደዱ የተነሳ የእመቤቴ ምስጋናዋ እንደሰማይ ኮከብ እንደ ባህር አሸዋ በዝቶልኝ እንደልብስ ለብሼው እንደ ምግብ ተመግቤው ጠግቤው እያለ ሲመኝ ይኖር ነበር፡፡ የሹትን መግለጽ እግዚአብሔር ልማዱ ነውና፡፡ ገልጾለት ፼ ካ4 ሺህ ድርሰት ደርሷል አኃዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ እስኪል ድረስ፡፡ የሚጸልየውም ጸሎት ከሉቃስ ወንጌል ወበሳድስን ጸሎተ እግዝእትነ ማርያምን አውጥቶ ፷4 ፷4 ጊዜ ይጸልይ ነበር፡፡ ከዕለታት በአንድ ቀን ዕለቱ ሰኑይ ጊዜው ነግህ ነው፡፡ የነግህ ተግባሩን አድርሶ ከመካነ ግብሩ ተቀምጦ ሳለ እመቤታችን ትመጣለች የብርሃን ምንጣፍ ይነጠፋል የብርሃን ይዘረጋል ከዚያ ላይ ሁና ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ ኤፍሬም ትለዋለች፡፡ እሱም ታጥቆ እጅ ነስቶ ይቆማል፡፡ ወድሰኒ ትለዋለች እፎ እክል ወድሶተኪ ዘኢይክሉ ሰማያውያን ወምድራውያን፡፡ ምድራውያን ጻድቃን ሰማእታት ሰማያውያን መላእክት አንቺን ለማመስገን የማይቻላቸው ለእኔ እንደምን ይቻለኛል አላት፡፡ በከመ አለበወከ መንፈስ ቅዱስ ተናገር አለችው፡፡ በተረቱበት መርታት ልማድ ነውና፡፡ እፎኑ ይከውነኒ ዝንቱ እንዘ እየአምር ብእሴ ብትለው፡፡ መልአኩ መንፈሰ እግዚአብሔር ቅዱስ ይመጽ ላእለኪ ብሏት ነበርና፡፡ ከዚህ በኋላ በርክኒ ይላታል፡፡ በረከተ ወልድየ ወአብሁ መንፈስ ቅዱስ ይኀድር በላእሌከ ትለዋለች፡፡ ተባርኮ ምስጋናዋን ይጀምራል፡፡ ሲያመሰግናትም ደቀ መዝሙር ቅኔ ቆጥሮ እንዲቀኝ ድርሰት አስቦ እንዲጽፍ አይደለም፡፡ ብልህ ደቀ መዝሙር ያጠናውን ቀለም ከመምህሩ ፊት ሰተት አድርጎ እንዲያደርስ እንደዚያ ነው፡፡ ስታደርሰውም ከሰባት ከፍላ አስደርዋለች፡፡ ስለምን ቢሉ በሰባቱ ዕለታት መመስገን ፈቃድዋ ቢሆን፡፡ አንድም ሰባቱ ዕለታት ምሳሌዋ ናቸውና በዕለቱ እሁድ ትመሰላለች፡፡ በዕለተ እሁድ አስራወ ፍጥረታት አራቱ በህርያት ተገኝተዋል፡፡ ከሷም ለዘኮነ ምክንያተ ፍጥረት በፍላዌሁ እንዲለው አስራወ ፍጥረት ጌታ ተገኝቷልና፡፡ በዕለተ ሰኑይ ትመሰላለች፡፡ በዕለተ ሰኑይ ከዚህ እስከ ብሩህ ሰማይ መልቶ የነበረውን ውሃ ከሶስት ከፍሎታል፡፡ አንዱን እጅ ከላይ ሰቅሎታል ሐኖስ ነው፡፡ አንዱን እጅ በዙርያው ወስኖታል፡፡ አንዱን እጅ አጽንቶ የብርሀን ማህደር አድርጎታል ጠፈር ነው ጠፈር የእመቤታችን ብርሃን የጌታ ምሳሌ፡፡ ይህማ የጠፈር ምሳሌ ሆነች እንጂ መቼ የዕለቲቱ ምሳሌ ሆነቻ ብሎ የዕለቲቱን የእሷ ጠፈር የእርሷ የተነሳው ስጋ ብርሃን የጌታ ምሳሌ፡፡ በዕለተ ሰሉስ ትመስላለች፡፡

በዕተ ሰሉስ ለታብቁል ምድር ሀመልማለ ሳእር ዘይዘራዕ በዘርዑ ወበበ ዘመዱ በበ አርአያሁ ወበበ አምሰሊሁ ባለ ጊዜ በእጁ የሚለቀሙ አትክልት በማጭድ የሚታጨዱ አዝእርት በምሳር የሚቆረጡ እፀዋት ለስጋውያን ምግብ የሚሆኑ ተገኝተዋል ከእሷም የመንፈሳዊያን ምግብ የሚሆን ጌታ ተገኝቷልና፡፡ በዕለተ ረቡዕ ትመሰላለች በዕለተ ረቡዕ ለይቁሙ ብርሃናት በቀጸ ሰማይ ባለ ጊዜ ለስጋው ያን ምግብ ጠየሚሆኑ ፀሃይ ጨረቃ ከዋክብት ተገኝተዋል፡፡ ከእሷም ለመንፈሳዊያን ምግብ የሚሆን ጌታ ተገኝቷልና፡፡ በዕለተ ሐሙስ ትመሰላለች በዕለተ ሐሙስ ለታወጽእ ባህር ዘቦ መንፈሰ ህይወት ባለ ጊዜ በልባቸው የሚሳቡ በእግቸው የሚሽከረከሩ በክንፋቸው የሚበሩ የደመ ነፍስ ህያዋን ሁነው የሚኖሩ ፍጥረታት ተገኝተዋል፡፡ በረው በረው የሄዱ አሉ ከዚም የቀሩ አሉ፡፡ በረው በረው የሄዱት የኢጥሙቃን ከዚያው የቀረት የጥሙቃን ምሳሌ፡፡ ያስወባርኮሙ ለክልኤሆሙ በአሃቲ በረከት ይላል ብሎ ብላባቸው የሚሳቡ የሰብአ ዓለም በእግራቸው የሚሳብ ከትሩፋት በደትሩፋት የሚሄዱ ባህታውያን በክንፋቸው የሚበሩ ተመስጦ ያላቸው የሰማዕታት ምሳሌ፡፡ ዕለቲቱ የሱዋ ባህር የጥምቀት ምሳሌ፡፡ በዕለተ አርብ ትመሰላለች በዕለተ አርብ በኩረ ፍጥረት አዳም ተገኝቷል፡፡ ዳግማዊ አዳም ጌታም ከእሳ ተገኝቷልና፡፡ በዕለተ ቀዳሚት ትመሰላለች፡፡ በዕለተ ቀዳሚት ስጋዊ እረፍት ተገኝቷል፡፡ ወእረፈ እግዚእነ እምኩሉ ዘአኃዘ ይግበር እንዲል ከሷም የመንፈሳውያን እረፍት ጌታ ተገኝቷልና ውዳሴ ዘሰኑይ ውዳሴ በአኑይ ውዳሴሃ ለእግዝእትነ መርያም ዘይትነበብ በዕለተ ሰኑይ ቡል በአንድ ነው ቃለ ጸሃፊ ነው፡፡ እሱ ግን ምስጋናዋን ፈቀደ እግዚእ ብሎ ይጀምራል፡፡ በእለተ ሰኑይ የሚነበብ የሚጸለይ የሚተረጎም አምላክን የወለደች የእመቤታችን ምስጋናዋ ይህ ነው ::
‹‹ፈቀደ እግዚእ ያግዕዞ ለአዳም ኁዙነ ወትኩዘ ልብ፡፡››
እምስት ሺህ ከ5፻ ዘመን በግብርና ዲያብሎስ የነበረ አዳምን ነጻ ያደርገው ዘንድ ወደደ፡፡ ህዙነ ልብ ትኩዘ ልብ ሲል ነው፡፡ ተምያጠ ወተውላጠ ህላዌያት ጽጌያት ወፍያት ትሩፋት ስመ ወግብረ ወልድ እንዲል፡፡ ወክብረ ወልድም ይላል፡፡ አንድም ያዘነ የተከዘ ሊያድነው ወደደ አዳምን የቤተ ፊት ልማድ አላገኘውም፡፡ ቤተ ፈት በዚህ ጊዜ እበላ እጠጣ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ተድላ ደስታ አደርግ ነበር እያለ ያእናል እርሱ ግን አትብላ ያለኝን እጸ በለስ በልቼ ከፈጣሪዬ ትእዛዝ ወጣሁ ብሉ ነውና፡፡ በአልቦቱ ካልእ ኅሊና ዘንበለ ብካይ ላዕለ ኃጢያቱ እንዲል አንድም ጌታ ያዘነ የተከዘ ሆኖ አዳምን ነጻ ሊያወጣው ወደደ፡፡ ተከዘት ነፍስየ እስከ ለሞት እንዲል አመስግነኝ ብትለው ምነው ወደ ሌላ ሄደ ቢሉ፡፡ ወደ ሌላ መለሄዱም አይደል አዳምን አስከትላው መጥታ ነበር እና ቢያየው አነሳው፡፡ አንድም ነገር ከስሩ ውሃ ከጥሩ እንዲሉ አዳም አባቷ ነውና፡፡ ከጥንት ጀምሮ ተርኮ ለመናገር ይሏል፡፡ ያስ ቢሆን ስለመን ፈቀደ እግዚእ አለ ቢሉ መክበሪያዋን ሲሻ ከዚያ ሁሉ ታኦፊላ ሊቃስን ዜና ሐዋርያትን ፅፈሕ ስደድልኝ ቢለው እም ጊዜ እርገሩ ለእግዚእነ እናዳለ መክበሪያቸው ሲሻ፡፡
‹‹ወያግብኦ ኀበ ዘትካት መንበሩ፡፡››
ወደ ቀደመ ቦታው ወደ ቀደመ ክብሩ ይመልሰው ዘንድ ወደደ ክብር ቢሊህ ልዩነት ቦታ ቡሉ ገነት ፍጡር ከሆነ ያለ ቦታ መኖር አይቻለውምና ከዚያውም ዘንድ ካለመደው የለመደውን ቢሰጡት ደስ ይለዋልና ይህማ ለሰማይና ለምድር ምን ቦታ አላቸው ቦታቸው እርሱ አይደለምን አሀዜ ዓለም በእራሁ ኩሉ እሁዝ ውስጥ እዴሁ ይጸውር ድደ ወነብር ጠፈር እንዲል ለሰማይና ለምድር ምን ቦታ አላቸው ቦታቸው እሱ አይደለምን ቢሉ የዕርቅ ምልክት ነው ንጉስ የተጣላውን የሳናፊልህን አትታጠቅ እንዲህ ካለ ቦታ አትውጣ ብሎ ወስኖ ያግዘዋል በታረቀው ጊዜ ርስቱን ጉልበቱን ቤቱን ንብረቱን ይመልስለታል እንደዚህም ሁሉ የዕርቅ ምልክት ነው፡፡
‹‹ሰአሊ ለነ ቅድስት፡፡››
5 ሺሕ ከ5፻ ዘመን በግብርናተ ዲያብሎስ የነበረ አዳምን ነፃ ካደረገው ልጅሽ እመቤታችን ንጽህት በድንግልና ጸጋው ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን ቅድስት አለ ንጽህት ጽንዕት ክብርት ልዩ ሲል ነው ንጽህትም አለ ሌሎች ሴቶ ከነቢብ ከቢር ቢነጹ ከኃሊዮ ዓየነጹም ርሷም ነቡብ ከገቢር ከሀልዮ ንጽህት ናትና፡፡ ወኢርኩሰት በምንትኒ እንዘፈጠራ ድንግል በህልናሃ ወድንግል በሥጋሃ አንዲል፡፡ ጽንዕትም አለ ሌሎች ሴቶች ቢጸኒ ለጊዜው ነው ኋላ ግን ተፈትሆ አለባቸው፡፡ እርሷ ግን ቅድመ ጸኒስ ቅድመ ወሊድ፤ ጊዜ ወሊድ ድህረ ወሊድ ጽንዕት ናትና ክብርትም አለ ሌሎችን ሴቶች ብናከብቸው ጻድቃንን ሰማዕታትን ወለዱ ብለን ነው እርሷ ግን ወላዲተ አምላክ ብለን ነውና ልዩም አለ እናትነትን ከድንግልና አስተባብራ የምትገኝ ከእመቤታችን በቀር ሌላ ሴት የለችምና፡፡ ዓይኑ ዐ ቢሆን አእመንሮው ለብዎውን ሳይብን አሳድሪብን፡፡ አላፋው አ ቢሆን ለምኚልን ማለት ነው፡፡ ልመናስ ከዚያ በኋላ እንኳን በእሷ ሌሎችን የለባቸውም በቀደመ ልመናዋ የምታስምር ስለሆነ እንዲህ አለ እንጂ ሰአሊ ለነ ቅድስት፡፡ ማን ተናግሮታል ቢሉ ኤፍሬም ተናግሮታል ይኽማ እንዳይሆን በግብጻውያን መጽሐፋቸውን በቃላቸው አይገኝምእሳ ብሎ ቅዱስ ያሬድ ለዜማ መክፈያ ተናግሮታል አንድም የኋላ ሊቃውንት ተናግረውታል
‹‹ሰረቀ በስጋ እምድንግል ዘእንበለ ዘርአ ብእሲ ወአድሀነነ፡፡››
ብረሃን ብሎ የሚመጣ ነውና እንደ አርእስት ሰረቅ ብሎ አነሳ ፈቀደ ብሎ ነበርና ወዶም አልቀረብ ዘር ምክንያት ሳይሆነው ከድንገል በስጋ ተወለደ፡፡ ተወልዶም አዳነን፡፡ በስጋ አለ በመለኮቱ አትወልደውምና፡፡ አኮ ወልደ ማርያም በመለኮቱ አላ በከመ ስርዓተ ትስብእቱ እንዲል፡፡ ልደቱ ለዘርያላደረገው እንደበለ ዘርእ ያደረገው ስለምን ነው ቢሉ ቀዳማዊ ልደሩን ለመግለጽ 5ሺህ ከ5፻ ዘመን ኢፈጸም ከእመቤታችን ያለ አባት መወለዱ ቅድመ ዓለም አብ ያለ እናት እንደ ተወለደ ይጠየቃልና፡፡ ልደት ቀዳማዊ ተዓውቀ ወደኃራዊ እንዲል፡፡ ዳግመኛም በዘርዕ በሩካቤ ተዋልዶ ቢሆን እርቅ ቢእሲ ባሉት ነበርና፡፡ ሶበሰ ተወለደ በሩካቤ ብእሲ ውቢእሲት ዘከማየ ብዙኃን እምተሃዘብዎ ወዕምረ ሰይዎ ሀሰት እንዲል፡፡ ያውስ ቢሆን ተፈትሆ ካላት ያላደረገው ተከሌላት ያደረገው ስለምን ነው በሉ ትንቢቱ መሳሌው ሊፈጸም፡፡ ተንቢት ናሁ ደንግል ትጸንስ ልትወልድ ወልደ ተብሎ ተነግሯል ምሳሌው አዳም ከህቱም ምድር ተገኝቷል፡፡ ጌም በህቱም ማኅጸን ለመወለዱ ምሣሌ፡፡ ሄዋን በህቱም ገቦ ተገኝታለች ጌታም በህቱም ማኅጸን ለመወለዱ ምሣሌ፡፡ ቤዛ ይስሃቅ በግዕ ከእህቱ ጉንድ ተገኝቷል ቤዛ አለም ክርስቶስን በእህቱ ማህጸን ለመወለዱ ምሳሌ፡፡ ጽምዐ እስራኤልን ያበረደ ውሃ ከህቱም እብን ተገኝቷል ጽምዐ ነፍሳትን ያበረደ ማየ ሕይወት ጌታን በህቱም ማህጸን ለመገኘቱ ምሣሌ ጽምዐ ሶምሶንን ያበረደ ውሃ በህቱም መንሰከ አድግ ተኝቷል ጽንዐ ኃጢያትን ያበረደ ማየ ሕይወት ጌታን በህቱም ማህጸን ለመገኘቱ ምሳሌ ትንቢቱን አውቆ አናግሯል ምሳሌውንም አንዲህ አውቆ አስመስሏል ፍጻሜው እንደምነው ቢሉ ከመ ትኩን መራሀተ ለሀይማኖት አባይ አንጂ ይላታል ብትወለደው ማህተመ ደንግልናዋ እንዳለተለወጠ ሰው ሲሆን አምላክነቱ ላለመለመጡ ድንግል ወሰብእ ሲባል ለመኖሩ ምሣሌ ነውና፡፡ ‹‹ሌሄዋ አንተ አስኃታ ከይሲ›› ከይሲ ባሳታት በሄዋን ምነው ከይሲ አለ ዲያብሎስ አይደለም ያሳታት ቢሉ በልሳኑ ከይሲ ተሰውሮ ነውና አንደም በማህደሩ ከይሲ አለው ህዳሪ በማህደር ማህደርን በህዳሪ መጥራት ልምድ ነውና አንድም በግብሩ ከይሲ አለው እባብ በመርዙ እንዲጎዳ ዲያብሎም በግብሩ በነገሩ ይጎዳልና፡፡
‹‹ፍትሀ ላእሊሀ እግዚአብሔር እንዘ ይብል ብዙህ አብዝኖ ለህማምኪ ወለጸአርኪ፡፡››
ጻርሽን ጋርሽን ምጥሽን አበዛዋለሁ ብሎ ከፈረደባት በኋላ በህማም ለዲ ወለድኪ ይኩን ምግባ እኪ ህበ ምትኪ አንዲል፡፡
‹‹ዘምረ ልቡ ኅበ ፍቅረ ስብእ ወአግአዛ፡፡››
ሰውን ወደደና ዋዌውን ታግሶ (አግአዛ) ነጻ አደረጋት ፍቅር አሀቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ በአብጸሆ እስከ ለሞት እንዲል ሄዋን ምክንያተ ስህተት ናት ከሲኦል አልወጣችም የሚሉ መናፍቃን ነበሩና በገአዛ አላባቸው አንድም አስከትላት መጥታ ነበርና ቢያያት አነሳት፡፡
‹‹ሰአሊ ለነ ቅድስት፡፡››
ሄዋንን ነጻ ካደረ ልጅስ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጻጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኚልን እየሱስ ክርስቶስ ቃል ዘተሰብዐ ፈቃደ ሰምረ ያልኩት ሰው የሆ ነው እየሱስ ክርስቶስ ነው ይህም ስም ብቻ የመለኮት ብቻ የትስብ እናት ስም አይደለም ከሁለት አካል አንድ አካል ሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ ቢሆን ከሁለት ባህርይ በሆን የወጣት ስም ነው እንጂ፡፡ ወእነግር አነሂ ከመ ይመፍትው እስምዮ በቃለ እግዚአብሔር ክርስቶስ ዘእምበለት ትስእብት ወኢ ለትስብእት ዘንበለ መለኮት ክርስቶስ የሰመይ ወእም ቅድመ ትስጉት አልቦ አይሰምዮ በዝንቱ ስም ልቃለ እግዚአብሐየር ክርስቶስ አንዲል፡፡
‹‹ ማህደረ ላእሌነ ፡፡››
ተሰብአና ኃደረ እንደ አለቀና እንደ ጠበቃ ይጠባበቃሉ ኃደረ ያለውን ይዘው ኀድረት እንዳይሉበት ተሰበአ አለባቸው፡፡ ተሰብአ የለውንም ይዘው ተለወጠ እንዳይሉበት አልነሣም ምትሐት ሥጋ በቅድምና ነበረ ባሕርዮን አግዝፎ ታየ የሚሉ መናፍቃን አሉና ላዕሌነ አለባቸው፡፡ ወውስቴትነ ይላል በጽርዕ ምላሹ፡፡ እንደ መስኖ ውሃ ገብቶ ወጣ የሚሉ መናፍቃን አሉና ስጋንም ነፍስንም እንደተዋሃደ ለመጠየቅ ላእሌነ ወውስቴትነ አለባቸው፡፡
‹‹ ወርኢነ ስብሀቲሁ ከመ ስብሀተ አሐድ ዋህድ ለአብሁ፡፡››
ለአባቱ እንደ አንድ ልጅ የሚሆን ክብሩን አየንለት፡፡ ለአባቱ አንድ ልጅ የሆነ ደጅ አፍ የመሰለው ማጀት የጎረስው ሁሉ ገንዘቡ ነው ለእርሱም የአብ ገንዘብ ሁሉ ገንዘቡ ነውና እስመ ኩሉ ዘቦ ለአቡየ ዚአየ ውእቱ እንዲል፡፡ አንድም ለአባቱ እንደ አንድ ልጅነቱ የሚሆን ክብሩን አየንለት ወይሰገድ ከመ ዋህድ እንዲል አንድም ያባቱን ጌትነት በደብረ ሲና እንዳየ የእርሱንም ጌትነት በደብረ ታቦር አየንለት አንድም አባቴ ኤልያስ አድሮ አንድ ምውት ኤልሳእ አንድሮ ሁለት ምውት ሲያስነሳ እንዳየነው፡፡
እሱም ስጋን ተዋህዶ የአራት ቀን ሬሳ አልአዛርን ሲያስነሳ አየነው የብሉይንም ለአብ የሐዲሱን ለወልድ ሰጥቶ አድሎ መናገር ልማድ ነው እንጂ፡፡ ሁሉም በሁሉ አሉ ያውስ ቢሆብ ወዴት ነበርና ርኢነ አለ ቢሉ የብረሉይን የእነሙሴን ዓይን አድርጎ፡፡ የሃዲሱን የእነጴጥሮስ ዓይን አደርጎ ከዚያ ሁሉ አባ ህርያቆስ ንህነ እሙንቱ እለ በላዕነ ምስሌሁ እምድኀረ ትንሣኤሁ አንዳለ፡፡ የሓዋርያትን መብል መብል አደርጎ፡፡
‹‹ ሠምራ ይሣዐለን፡፡››
ይቅር ይለን ዘንድ ወደደ ሦስት ጊዜ ፈቀደ ሠምረ እለ ለአዳም ለሔዋን ለሕፃናቱ፡፡ ለሥጋ ለነፍስ ለደመ ነፍስ እንደ ካሰ ለማጠየቅ
‹‹ ሰአሊ ለነ ቅድስት፡፡››
ይቅር ይለን ዘንድ ከወደደ ለ3ጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን አንዳነሣን ለምኚልን፡፡
‹‹ርእየ ኢሳይያስ ነቢይ በመንፈስ ትንቢት የምስጢር ለዓመኑኤል፡፡››
ነቢዮ ኢሳያስ ትንቢት በሚገልጽ በመንፈስ ቅዱስ የዐደማኑኤልን ምሥጢር አየ አጸና፡፡
‹‹ ወበእንተዝ ጸርሐ አንዘ ይብል፡፡›› ስዚህ ነገር አሰምቶ ተናገረ፡፡ ዐማኑኤል መለት ሰው የሆነ አምላክ ማለት ነው አዝ ስም ዐቢይ ጥቀ ወአይደሉ ፈሊጦቶ አንዲል፡፡ ጸርሐ አለ ጮሆ የተናገሩት ከሩቅ እንዲሰማ ነገሩ ጽንፍ እሰከ ጽንፍ ይደርሰልና፡፡ ጸርሐ አለ አንጂ ተናገረ ሲል ነው፡፡
‹‹ ሐፃን ተወልደ ለነ፡፡››
ሕፃን ተወለደልን፡፡
‹‹ውልድ ተውሃበ ለነ፡፡››
ወልድ ለሕማም ለሞት ተሰጠልን አንድም ወልድ ተውሀበ ለነ ለኩነተ ሥጋ ተሰጠልን ወሕፃን ተወልደ ለነ ሕጻንም ሆኖ ተወለደልን፡፡ ለመለኮት የአካልም የክብርም ሕፀፅ ነበረበት ሥጋ ምላት ሆነው የሚሉ መናፍቃን ነበሩና ለነ አለባቸው ለርሱ ቢሆን ሎቱ ይል ነበር፡፡ ይህም ደበአርዮስ ያሳይበታል፡፡
‹‹ ሰአሊ ለነ ቅድስት፡››
ወልድ ዘበላዕሉ ሕጸን ዘበታህቱ ከሚባል ልጅሽ እመቤታችን ጽንዕጽ በድንግልና ጸጋውን ክብሩን አንዲያሣ ለምኚልን፡፡
‹‹ ተፈሣሕ ወተሐሠይ ኦ ዘመደ ዕጓለ እመሕያው፡፡››
ባሕርየ ዕጓለ እመሕያው በውሰጥ በአፍአ በነፍስሰ በሥጋ ደስ የበልህ፡፡
እሰመ አፍቀሮ እግዚብሔር ለዓለም፡፡
እግዚአብሔር ሰውን ወዶታልና፡፡
‹‹ ወመጠወ ወልዶ ዋህደ፡፡››
ልጁን ለሕማም ለሞት እስከ መስጠት ደርሶ፡፡ አንድም ወዶ ምን አደረገለት፡፡ ትለኝ እንደሆነ ተቀዳሙ ተከታይ የሌለው ልጁን ለሕማም ለሞት አሳልፎ እግዚአብሔር ለዓም፡፡ እስከ ወልዶ ዋሕደ መጠወ ወወሀበ ቤዛ ኩሉ እንዲል፡፡
‹‹ ከመ ይሕየው ኩሉ ዘየ አምን ቦቱ እስከ ለዓለም ››
ይሕየው እስከ ለዓለም ኩሉ እሰከ ለዓለም ዘየአምን እስከ ለዓለም ብሎ ይገጥሟል፡፡ ኩሉ እስከ ለዓለም እስከ ምጽአት ድረስ የሚነሣ ትውልድ ሁሉ፡፡ ዘየአምን እስከ ለዓለም እስከ ምጽአት ድረስ የሚያምንበት አለ ከዚያ በኋላ ያመኑት እምነት ኤጠቅምምና፡፡ ከዚያ በኋላስ አይሁድስ እንኳ እፎኑ ርእር ታመጽእ አሚነ እንዲል እ ኮነ ወልደ ዕጓለ እመሕያው ወለቅዲሳን ኮነት ርስቱ ይላሉ አይጠቀሙበትም እንጂ፡፡ ይሕየው እስከ ለዓም ፍጻሜ የሌለው እስከ ነው ኢተመይጠ ቋዕ እስከ አመ ነትገ ማየ አይኀ፡፡ ኢወለደት ሜልኮል እሰከ አመ ሞተት እንዲል፡፡
‹‹ፈነወ ለነ መዝራዕቶ ልዑለ›› ልዑል ክንዱን ረቂቅ ክንዱን ሰደደልን ፈነወም ቢል በሥጋ ነው እንጂ በመለኮቱ አይደለም እፎኑ የፌንዎ በመለኮቱ ዘእንበለ ዳዕሙ በትስብእቱ ዘነሥኦ በአምሳሌ ላዕከ ይፌንዎ በአምሳለ ላእከ እንዲል፡፡ ክንድ አለው የሰው ኀይሉ በክንዱ እንዲታወቅ የአብም ኀይሉ በወልድ ታውቋልና፡፡ አንድም ክንድ ከአካል ሳይለይ የወደቀውን ዕቃ አንሥቶ ይመለሳል እርሱመ ከአብ አንድነት ሳየለይ አዳምን አድኗል፡፡ አንድም በከንድ የራቀውን ያቀርቡባል የቀረበውን ያርቁበታል በርሱም ጸድቃንን ንሁ ኃቤየ ብሎ ያቅርብበታል ኃጥአንን ሑሩ እምኔየ ብሎ ያረቅበታልና፡፡
‹‹ ሰአሊ ለነ ቅድስት፡፡››
እዱ መዝራዕቱ ከሚባለው ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኝልን፡፡
ዘሀ ሎ፡፡
እምቅመ ዓለም የነበው፡፡
ወይዘሉ፡፡
ዓምን አሳልፎ የሚኖረው፡፡
አመጸአ፡፡
ለኪነት ሥጋ የመጣው፡፡
‹‹ ወካዕበ የመጽእ ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ዘተሰብአ እምኔኪ ዘእነበለ ውላጤ፡፡››
ዳግመኛ ዓለሙን ለማሳለፍ የሚመጣው፡፡ ካንች ሳይለወጥ ሰው የሆነው አምላካዊ ቃል ኢየሱስ ክርሰቶስ፡፡
‹‹ ኮነ ፍጹመ ሰብአ፡፡››
ፍጽም ሰው ሆነ፡፡ ሰው የሆነውን ሰው ሆነ ማለት መንድር ነው ቢሉ ፍጹመ ለማለት ደገመው፡፡ አንድም ዘሀሎ፡፡ እምቅድመ ዓለም የነበረው ወይሄሉ፡፡ ዓለሙን አሳልፎ የሚኖረው ነው፡፡ ዘመጽአ፡፡ ዓለሙን አሳልፎ የሚኖረው ለኪነተ ሥጋ የመጣው ነው፡፡
‹‹ ወከዕበ የመጽእ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ዘተሰብአ ዘእንበለ ውላጤ፡፡››
ለኩነተ ሥጋ የመጣው፡፡ ዳግመኛ ዓለሙን ለማሳለፍ የሚመጣው ነው፡፡ ደግመኛ ዓለሙን ለማሳለፍ የሚመጣው፡፡ ካንች ሳይለወጥ ሰው የሆነው አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ኮነ ፍጹመ ሰብአ፡፡ ፍጸም ሆነ፡፡ ትቅስ ወኢተዋሐደ በመንፈቀ ህላዌ በኢኮነ ካልአ እንስሳ ዘበአንትጎ፡፡ አላምሉዕ ወፍጹም ውእቱ በአሐዱ ሀላዌ የገብር ዘክልኤቱ ህላዌያት እንዲል፡፡ ከዚህ ነፍስ አልነሣም፡፡
ምትሐት ኀድት፡፡ ተለወጠ የሙሉ መናፍቃን አሉና ለዚህ ያመታል፡፡
‹‹ ኢተበዓደ ወኢተፈልጠ በኪሉ ግብሩ ወልድ ዋሕድ፡፡››
አሁን ነፍስ አልነሣም ምትሐት ላሉት ይመልሳል፡፡ ተቀዳሙ ተካታይ የሌለው ወልድ ዋሕድ በሥራው ሁሉ ከኛ አልተለየም፡፡
‹‹አላ አሐዱ ራእይ፡፡››
አንድ ግብር ነው እንጂ፡፡
‹‹ወአሐዱ ህላዌ፡፡››
አንድ ባሕርይ ነው እንጂ፡፡ ወአሐዱ፡፡
አንድም ነው እንጂ፡፡
ሠስት ጊዜ አሐዱ አሐዱ አሐዱ አለ በሦስት ወገን የመስለናል በኀይለ ዘርዕ በኀይለ ንባብ በኀይለ እንስሳ፡፡
‹‹ መለኮት ዘእግዚአብሔር ቃል፡፡››
አካላዊ ቃል አንድም አሁን ጎድረት ላለው ይመልሳል፡፡ ተቀዳሜ ተከታይ የሌለው ወልድ ዋሕድ በሥራው ሁሉ ከነሣው ሥጋ አልተለየም፡፡
‹‹ አላ አሐዱ ራእይ፡፡››
አንድ ግብር ነው አንጂ፡፡
ወ1ዱ ህላዌ አንድ ባሕርይነው እንጂ፡፡
‹‹ ወአሐዱ መለኮት፡፡››
አንድ አካል ነው እንጂ፡፡
እስመ 3ቱ ኁልቁ መለኮቱ እንዲል፡፡ እንድም ተለወጠ ላሉት ይመልሳል፡፡ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ወልድ ዋሕድ ሰውም ቢሆን ከአብ ከባሕርይ አባቱ ከመንፈስ ቅዱስ ከባሕርይ ሕይወቱ አለተለየም፡፡
እላ አሐዱ ራእይ፡፡
አንድ ኀብረ መልክእ ነው እንጂ፡፡ ወአሐዱ ህላዌ፡፡ አንድ ባሕርይ ነው አንጂ፡፡ ወአሐዱ መለኮት፡፡ አንድ አገዛዝ ነው አንጂ፡፡ ውስተ ኩሉ በሐውረት መለኮቱ እንዲል፡፡
‹‹ ዘእግዚአብሔር ቃል፡››
አካላዊ ቃል፡፡
‹‹ ሰአሊ ለነ ቅድስት፡፡››
ይቆየን የዕለተ ሰኞ ክፍል 2 በሚከጥለው ሳምንት ይቀጥላል:: ............ቸር ያቆየን!!!!!

Saturday, August 7, 2010

ውዳሴ ማርያም አንድምታ በዕለተ ሰንበት እሁድ ክፍል 1

ውዳሴሃ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ዘይትነበብ በዕለተ ሰንበተ ክርስቲያን::
ሰንበት አይሁድ አለችና ከዚያች ሲለይ ሰንበተ ክርስቲያን አለ :ያውስ በከንቱ ነውን ወበዛቲ ዕለት እሙነ ተፈጸመ እንዲል ሁለቱን ቀን የሚያከብር የሆነ እንደሆነ ዓርብ ከሰዓት ይወጣል እሁድ በሰዓት ይወርዳል::አንዱን ቀን የሚያከብር እንደሆነ ቅዳሜ ከሰዓት ይወጣል እሁድ ከሰዓት ይወርዳል: እንዲህ እያለ ሲኖር ጌታ የሚመጣው በዕለተ እሁድ ነውና እንደወጣ ይቀራል: በዚህም ቀን እመቤታችን ከወትሮው ጊዜዋ ቀደም ብላ መጥታ ለምንት ኢወደስከኒ በዛቲ ዕለት አለችው ከወትሮው ጊዜዋ ቀደም ብላ ከመጣች ስለምን ለምንት ኢወደስከኒ አለችው ቢሉ የህሊናውን አውቃ: እሱም በገድል ተቀጥቅጦ ነዋሪ ስለሆነ ጥቂት ወይን ጠጥቶ ዕረፍት ሽቶ ነበርና: ጳውሎስ ጢሞትዮስን ህዳጠ ወይነ ቶስሕ በእንተ ሕማመ ከብድከ ወበእንተ ደዌከ ዘዘልፍ እንዳለው:ዛቲ ዕለት ዓባይ ወክብርት አላት: ዛቲ ዕለት ተዓቢ እምኩሎን ውዳሴያት አለችው ከዚህ በኋላ ባርክኒ ይላታል በረከተ ወልድየ ወአቡየ ወመንፈስቅዱስ ይህድር በላዕሌከ ትለዋለች: ተባርኮ ምስጋናዋን ይጀምራል በዚህም ቀን በቤተ መቅደስ ባሉ ንዋያት በመሶብ ወርቅ በማዕጠንተ ወርቅ በበትረ አሮን እየመሰለ ሲያመሰግናት አድሯል ::
"ተሰመይኪ ፍቅርተ ኦ ቡርክት እምአንስት:አንቲ ውእቱ ዳግሚት ቀመር እንተ ትሰመይ ቅድስተ ቅዱሳን: ወውስቴታ ጽላተ ኪዳን:"
ንዕድ ክብርት ሆይ ከሴቶች ተለይተሽ የሥላሴ ባለሟል ተባልሽ : ከተለዩ የተለየሽ ከከበሩ የከበርሽ ቅዱሳን ኪሩቤል የተሳሉብሽ ቅዱሳን ካህናት የሚያመሰግኑሽ ሁለተኛ ክፍል አንቺ ነሽ: ህግ የተጻፈባት ጽላት ያለብሽ ሕጉን ኪዳን ይለዋል ብትጠብቁት ይጠብቃችኋል ብሎ ተከይዶበታልና::
"10ቱ ቃላት እለ ተጽሕፋ በአጻብዒሁ ለእግዚአብሔር: ቀዲሙ ዜነወነ በየውጣ እንተ ይእቲ ቀዳሜ ስሙ ለመድሃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ::"
ኪዳንም ያልሁት በአፃብዐ እግዚአብሄር የተጻፉ ዐሥሩ ቃላት ናቸው በግብር አምላካዊ ስለተገኙ በአፃብዐ እግዚአብሄር አለ: ከስመ ሥጋዌም የሚቀድም ስሙን በየውጣ ነገረን: ከስመ ስጋዌ የሚቀድም ስሙን : ኢታምልክ ባዕደ አምላክ ዘእንበሌየ ብሎ በዮድ ፊደል ነገረን አለ: ዮድ ለአሌ ዐሥረኛ እንደሆነች ኢታምልም ለኢትፍቱ ዐሥረና ናትና: አንድም ከስመ ሥጋዌው የሚበልጥ አሙን በየውጣ ነገረን አለ:ቀዳሜ ፍጥረት ብሄሞት ቀዳሚሆሙ ለአህዛብ አማሌቅ እንዲል: የውጣ በሃገራቸው ዕዝል ቅጽል የላትም አንድ ጭራ ናት: ዐሠርቱም በሃገራችን ዕዝል ቅጽል የላትም አንድ ጭራ ናትና: አንድም ዋሕድ ቃለ እግዚአብሔር በአፃብዐ መንፈስቅዱስ በማህጸኑዋ እንዲቀረጽ ዐሠርቱ ቃላትን በጽላቱ ጽፎ በማኖሩ ነገረን:ታሪክ:- እስራኤል ከግብጽ ከወጡ በኋላ ሙሴ አሮንና ሖርን ከተማ ጠባቂ አድርጎ ኢያሱን አስከትሎ ደብረሲና ሄዶ ስድስት ቀ ቃል ለቃል ይነጋገረዋል: ሠላሳ ዐራት ቀን በልቦናው የሳለበትን እየነገረ ያጽፈዋል: ከዚህም በኋላ ሙሴ ቢዘገይባቸው እስራኤል ከአሮን ዘንድ ሄደው አሮን አሮን ግበር ለነ አማልክተ እለ የሐውር ቅድሜነ ወእለ ይፀብዑ ፀረነ እስመ ዝኩሰ ሙሴ ዘአውጻነ እምድረ ግብጽ ኢነአምር ከመ ምንተ ኮነ :አመሌ አመሌ ሲል ደብረ ሲና ያየው እሳትም በልቶት እንደሆነ ወደ ኤርትራ ተመልሶ ሄዶ አስጥማው ቀርቶም እንደሆነ ሙሴ የሆነውን አናቅምና ጣዖት ስራልን አሉት: እሱም እምቢ ብላቸው እስራኤል ቁጡአን ናቸው በደንጊያ ወግረው ይገድሉኛል: ይሁንም ብላቸው ፈጣሪዬ ይጣላኛል ብሎ እስራኤል ሃብት ወዳጆች ናቸው ከዛሬ ነገ ሲሉ ወንድሜ ይመጣልኛል ከነገር እድናለው ብሎ ሴቶችንም ወንዶችንም ከግብጽ ያወጣችሁትን ገንዘባችሁን አምጡ አላቸው: ሰይጣን አነሳስቷቸዋል እና እንዋል እንደር ሳይሉ ዕለቱን አመጡለት ጉድጓዽ አስምሶ እሳት አስነድዶ ከዚያ ላይ አስጣለው: ከዚህ በኋላ አንድ ቀንዱ የወርቅ አንድ ቀንዱ የብር ጅራቱ የሃር የሆነ ምስል መቶ ቆመ:ይህስ ምትሃት ይመስላል ብሎ ተድበልብሎ ወጣ እሱ ቅርጽ አውጥቶ አሰርቶታል::
ከዚህ በኋላ በፍና ተሳልቆ ጌሰም በዓለ እግዚእ ብሎ አዋጅ ነገረ : ከዚህ በኋላ መስዋዕቱን በልተው ሲዘፍኑ ሲያጨበጭቡ: ሙሴ ሙሴ አበሱኒ እስራኤል ሕዝብከ:አለው ጸብ ተጀመረ ህዝብየ ይላቸው የነበረ ሕዝብከ አለው አባት ልጁን ሲጣላ ያ ልጅሽ እንዲህ አደረገ እንዲል:ሰንኪያስ ወርደህ ሥራ ቅፃ አለው: ከዚህ በኋላ ዓሥሩን ቃላት በጽላት ጽፎ ሰጠው ያን ተቀብሎ እያሱን አስከትሎ ሲሄድ እስራኤል ጉሽ ጠጅ ጠጥተው ይዘፍናሉ ያጨበጭባሉ: የአርበኛ የሰልፈኛ ድምጽ አይደል አለው;ቢደርስ ከዚያ ጣዖቱን አቁመው ተረፈ መስዋዕቱን በልተው ሲሰግዱ አየ ቢደነግጥ ከእጁ ወድቆ ጽላቱ ተሰበረ: ዛሬ ከቄስ እጅ ጥና ወድቆ እንዲሰበር አንድም በጽላቱ ጣዖቱን መታው ጣዖቱም ጽላቱም ተሰበረ ከዚህ በኋላ ወርቁን አስፈጭቶ ከፈሳሽ ባህር አስበጥብጦ ጠጡ አላቸው: ፍቅረ ጣዖት ያደረበት ከከንፈሩ ከግንባሩ እንደ ለምጽ ተቀረጸበት: ይህን ምልክት አድርጎ ሌዋውያንን ከበር አቁሞ በሏቸው አትማሯቸው: አባት ልጁን ልጅ አባቱን ወንድም ወንድሙን አይማረው ብሎ 3000ሺህ ሰዎች አስፈጅቷል: አንፈስክዎ ለእግዚአብሔር እስኪላቸው ድረስ: ከዚህ በኋላ ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክት ቀር ከመ ቀዳምያት አለው: የቀደመውን አስመስለህ አምጣ አለው ይዞ ሄዶ ቃሉ በግብር አምላካዊ ተገኝቷልና ይህውም ምሳሌ ነው: የቀደመው ጽላት የአዳም ሁለት መሆኑ የስጋውና የነፍሱ በግብር አምላካዊ መገኘቱ አዳም እንበለ ዘርዕ ለመገኘቱ ምሳሌ: የኋለኛው ጽላት የእመቤታችን ሁለት መሆኑ የስጋዋና የነፍሷ: ቀር ከመ ቀዳምያት አለው: እመቤታችን በዘር ለመገኘቷ ምሳሌ:ቃሉ የጌታ ምሳሌ በግብር አምላካዊ መገኘቱ: ጌታ እንበለ ዘርዕ ለመገኘቱ ምሳሌ: የቀደመው ጽላት የዕንቁ ነው የኋለኛው ጽላት ዕብነ በረድ ነው::
"ዘተሰብአ እምኔኪ ዘእንበለ ውላጤ:ወኮነ አራቄ ለሐዲስ ኪዳን:በውሂዘ ደሙ ቅዱስ አንጽሆሙ ለመሃይምናን ወለሕዝብ ንጹሃን:"
ካንቺ ሳይለወጥ ሰው የሆነ ለወንጌል ሊቀ ካህናት ለመንግስተ ሰማያት አስታራቂ ሆነ: ሐዲስ ኪዳን ወንጌል ብሉይ ኪዳን ኦሪት:ሐዲስ ኪዳን መንግስተ ሰማያት ብሉይ ኪዳን ምድረ ርስት: በከበረ ደሙ ፈሳሽነት በዓለመ ስጋ በዓለመ ነፍስ ያሉትን አዳናቸው: አንድም በዕለተ ዓርብ በቀኖት የፈሰሰውን ደሙን መላዕክት በአውራ ጣታቸው ተቀብለው እረጭተውታል:ይህንስ ያህል አይደፍሩም ብሎ በጽዋዓ ተቀብለውታል: ዛሬ ቤተክርስቲያን የሚሰራበት ደሙ የፈሰሰበት ቦታ ነው: ታሪክ:- ጳልቃን ጣልቃን የሚባሉ አዕዋፍ አሉ ልጆቻቸውን ይወዳሉተንከባክበው አቅፈው ያኖሩዋቸዋል ልጆቹ ተጫወትን ብለው ፊታቸውን ይጸፉታል ይሰማቸዋል ራሳቸውን ቆርጠው ይገድሏቸዋል ከዚህ በኋላ በሦስተኛው ቀን ከናታቸው ካባታቸው ጎን ቢሉ ደም አውጥተው ቀብተው ያስነሷቸዋል: ጳልቃን ጣልቃን የተባሉ ሥላሴ ናቸው ልጆቻቸውን ተንከባክበው እንዲያኖሩዋቸው በገነት አዳምንና ሄዋንናክብረው አኖሯቸው ተጫወትን ብለው ፊታቸውን እንዲጸፉ አምላክነትን ሲፈልጉ ተገኝተዋል: ራሳቸውንም ቆርጦ እንደመግደል በሞተ ስጋ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ርደተ ገሃነም ፈርደውባቸዋል በሦስተኛውም ቀንከናታቸው ካባታቸው ጎን ቢሉ ደም አውትተው ቀብተው እንዲያስነሷቸው: አንተ አቡነ ወአንተ እምነ የሚባል ጌታ ከጎኑ ደሙን አፍስሶ ለማዳኑ ምሳሌ " ሰአሊ ለነ ቅድስት"
በከበረ ደሙ ፈሳሽነት በዓለመ ስጋ በዓለመ ነፍስ ያሉትን ካዳነ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኚልን
"ወበእንተዝ ናዓብየኪ ኩልነ ኦ እግዝእትነ ወላዲተ አምላክ: ንጽህት ኩሉ ግዜ:ንስህል ወናንቀዓዱ ሃቤኪ :ከመ ንርከብ ሣህለ በሃበ መፍቀረ ሰብእ:"
መጽሃፍ ላለፈውም ለሚመጣውም አጸፋ ይሰጣል: አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ስለዚህ ነገር ሁላችን እናከብርሻለን እናገንሻለን:ንጽህት ኩሎ ጊዜ ንስህል ኩሎ ጊዜ ብሎ ይገጥማል: ሁልግዜ ንጽህት የምትሆኚ:ሁልጊዜ አይነ ልቦናችንን ወዳንቺ እንሰቅላለን: ሰውን ከሚወድ ሰው ከሚወደው ከርሱ ይቅርታን እናገኝ ዘንድ::
"ታቦት ዘወርቅ ልቡጥ እምኩለሄ ዘግብር እምዕፅ ዘኢይነቅዝ: ይትሜሰል ለ ዘእግዚአብሔር ቃል:"
ሸምሸር ሸጢን ከሚባል ከማይነቅዝ እንጨት የተቀረጸ በአፍአ በውስጥ በወርቅ የተለበጠ ታቦት: አካላዊ ቃልን ይመስልልናል አንድም መመሳሰል የጋራ ነው ብሎአካላዊ ቃል ታቦትን ይመስልልናል: ታቦት የእመቤታችን ምሳሌ: (ዕፅ ዘኢይነቅዝ) የአብርሐም:ዘኢይነቅዝ አለው በአምልኮተ ጣዖት አይለወጥምና: አንድም ታቦት የጌታ ምሳሌ ዕፅ ዘኢይነቅዝ የእመቤታችን ዘኢይነቅዝ አከ በሃጥያት አትለወጥምና አንድም ታቦት የጌታ ምሳሌ:ዕፅ ዘኢይነቅዝ የአብ: አሁን ዘግቡር ሲል ያውካል::
"ዘኮነ ሰብአ ዘእንበለ ፍልጠት ወኢውላጤ: መለኮት ንጹህ ዘአልቦ ሙስና:ዘዕሩይ ምስለ አብ: ወቦቱ አብስራ ለንጽህት::"
መለወጥ ሳያገኘው መለየት ሳያገኘው ሰው የሆነ:ንጹህ ከተፈልጦ ከተድህሮ አንድም ንጹህ ካለመመለክ ንጹህ የሚሆን መለወጥ የሌለበት በአብ ዕሪና ያለብባለመለወጡ አለመለወጡአን: ባለመለየቱ አለማለየቷን ነገራት: አንድም በዕጽ ዘኢይነቅዝ አንድም በገብርኤል አድሮ ነገራት::
"ዘእንበለ ዘርዕ ኮነ ከማነ በኪነ ጥበቡ ቅዱስ: ዘተሰብአ እምኔኪ ዘእንበለ ርኩስ: ደመረ መለኮቶ:"
ከጥበብ በሚበልጥ ጥበብ ዘር ምክንያት ሳይሆን እንደኛ ሰው ሆነ ከጥበቡ በሚበልጥ ጥበቡ አለ: ዓለሙን ከፈጠረበት ሰው ሆኖ ዓለሙን ያዳነበት ትበብ ይበልጣልና: አንድም በፍጹም ጥበቡ እንደኛ ሰው ሆነ: አደፍ ጉድፍ ሳያገኝሽ ከስጋሽ ስጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆነ: መለኮቱን አዋህዶ::" ሰአሊ ለነ ቅድስት::"
መለኮቱን አዋህዶ ሰው ከሆነ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን::ታቦትን ከዚህ ይናገራሉ ሸምሸር ሸጢን ከሚባል ከማይነቅዝ እንጨት አቆልቋዩ ሁለት ክንድ ከስንዝር ቁመቱ ክንድ ከስንዝር አድርገህ ታቦትን ቅረጽ ብሎታል: በአፍአ በውስጥ በወርቅ ለብጠው: አራት ቀለበት ሁለት መሎጊያ አብጅለት ብሎታል:ምስሐልንም ሁለት ክንድ ከስንዝር ሞላልነቱ ርሁቡ ክንድ ከስንዝር ቅረጽ ብሎታል የዚህ ቁመት የለውም ሁለቱን ኪሩቤል እንደሚናተፍ አውራ ዶሮ አስመስለህ ሳላቸውዙርያውን ፈለግ አውጥተህ የማይረጋ ብጽብጽ ወርቅ አፍስስበት አለው ይህውም ምሳሌ ነው: ሁለት ክንድ ከስንዝር ከአዳም እስከ ኖህ ያለው ዘመን ነው:2256 ይሆናል : በ2256 ዘመን አርአያ ድንግል ታቦተ ኖህ ለመገኘቷ ምሳሌ ነው: ክንድ ከስንዝር ቁመት ከኖህ እስከ ሙሴ ያለው ዘመን ነው 1600 ይሆናል: በ1600 ዘመን አርአያ ድንግል ታቦተ ሙሴ ለመገኘቷ ምሳሌ ነው: ክንድ ከስንዝር ርሁብ ከሙሴ ጀምሮ እስከ እመቤታችን ያለው ዘመን ነው: 1600 ይሆናል: በ1600 ዘመን ሐመረ ኖህ እና ታቦተ ሙሴ ምሳሌዋ የሚሆኑ አማናዊት ድንግል ለመገኘቷ ምሳሌ ነው: ታቹ የንጹሃን አበው ሁለት መሎጊያ የፍቅረ ቢጽና የፍቅረ እግዚአብሔር ምሳሌ ነው: ዐራት ቀለበት በርእይ በሰሚዕ በገሢሥ በአፄንዎ በዚህ ሁሉ ንጽህት ናትና: ዳሩና ዳሩ የሃና የኢያቄም ገቢይቱ (ግበቱ) የርሷ ምሳሌ ሁለቱ ኪሩቤል የመልአከ ዑቃቢና የመልአከ መበስር ምሳለ ነው; በአመት አንድ ቀንሊቀ ካህናቱ ገብቶ በሁለቱ ኪሩቤል መካከል ድምጽ ሰምቶ ይወጣ ነበር: እርሷም በመልአከ ዑቃቢ ተጠብቃ ከመልአከ መበስር ድምጽ ሰምታ ጌታን ጸንሳ ለመገኘቷ ምሳሌ ነው: አንድም የኦሪኒና የሶፍያ ምሳሌ ነው: ባስልዮስን ከነ አትለያቸው ሳላቸው ብላዋለችና:ናንድም የዮሴፍና የሰሎሜ ምሳሌ ነው:በመከራዋ ጊዜ አልተለዩአትምና ፈለግ የልቦናዋ ምሳሌ ብጽብጽ ወርቅ የሁከት መንፈሳዊ ምሳሌ ሁከት መንፈሳዊ ከልቦና አይደለምና::
"መቅደስ ዘይኬልልዋ ኪሩቤል እለ ሥዑላን በሥዕለ እግዚአብሔር:ቃል ዘተሰባ እምኔኪ አንጽሕት ዘእንበለ ውላጤ: ኮነ ሠራዬ ሃጥያት ወደምሳሴ አበሳነ ::"
እግዚአብሔር በፈጠራቸው በኪሩቤል አምሳል ሙሴ የሳላቸው ኪሩቤል የሚጋርዱሽ መቅደስ ሙሴ አንቺ ነሽ: አንድም እግዚአብሄር በፈጠራቸው ኪሩቤል አምሳል ሰሎሞን የሳላቸው ኪሩቤል የሚጋርዱሽ መቅደስ ሰሎሞን አንቺ ነሽ: አንድም ኦ መቅደስ ዘኮነ ለሊሁ እግዚአብሄር ሊቀ ካህናት እንዲል ጌታ በማህጸን ዘደረብሽ መቅደስ አንቺ ነሽ: ሣይለወጥ ካንቺ ሰው የሆነው አካላዊ ቃል: ስለ ስጋው ስለ ነፍስ ስለ ጊዜው ስለ ዘላለሙ: ይደጋግማል በውስት በአፍአ በነፍስ በስጋ ሃጥያታችንን የሚያስተሰርይልን ሆነ::" ሰአሊ ለነ ቅድስት"
ሃጥያታችንን ከሚያስተሰርይልን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን አሜን !!!!!:: ይቆየን የእሁድን ቀጣይ ክፍል በሚቀጥለው እሁድ..........ቸር ያቆየን!

ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ክፍል 2

5:- ወእቀውም ዮም በትህትና ወበ ፍቅር በዛቲ ዕለት ቅድመ ዝንቱ ምስጢር ግሩም: ዮምና በዛቲ ዕለት አንድ ወገን: ቀድሶ ያቆረበባት ቀን ናት: እንደጠሉኝ ልጥላቸው እንደናቁኝ ልናቃቸው ሳልል በፍቅር በትህትና ጸንቼ ግሩም በሚሆን በስጋው በደሙ ፊት እቆማለው:: ሐተታ:- ስጋው ደሙን ምስጢር አለው ከአምስቱ አዕማደ ምስጢር አንዱ ምስጢረ ቁርባን ነውና:: አንድም ከሃጥያት ነጽቶ ቢቀበሉት በልሳነ ነፍስ ያናግራልና:አንድም ሲለወጥ አይታይምና: ለበቁትም ሰዎች ስንኳ ከተለወጠ በኋላ ነው እንጂ ሲለወጥ አይታይምና: አንድም የወድያኛውን ምስጢር ይገልጣልና ግሩም አለ: በሚገባ ቢቀበሉት ግሩም ጸጋ ያሰጣልና: በሚገባ ባይቀበሉት ግሩም ፍዳ ያመጣልና: አንድም ግሩማን መላእክት ከበውት ይቆማሉና አንድም ከሃጥያት ነጽቶ ቢቀበሉት ግሩም ምስጢርን ይገልጻልና: አንድም የአምላክ ስጋ የአምላክ ደም አይገርም ማን ይገረም: አንድም የሚወደድ ሲል ነው: ኢትርዓይ ግርማ ርእየቱ ለኤልያብ እንዲል አንድም ልዩ ሲል ነው: ግሩም ምክሩ እመጓለ እመ ህያው እንዲል::
ወቅድመ ዝንቱ ማዕድ ወቁርባን ዐ ማእድም ያለው ስጋው ደሙ ነው: ሐተታ:- ማእድ አለው ማእድ ስጋዊን ከበው እንዲመገቡት ይህንም አእሩግ ህጻናት ከበው ይቀበሉታልና: አንድም ለማእድ ስጋዊ ሰው እንዲመረጥለት ለዚህም የበቃና ያልበቃ ይመረጥለታልና አንድም ማዕደ ነፍስ ነውና ቁርባን እንዳለፈው: አንድም ማእድ ጻህል ጽዋው ቁርባን ስጋው ደሙ ነው ::
6:- በአማን ቁርባን ውዕቱ ዘእይክሉ ይጥዐሙ እምኔሁ ግሙናነ መንፈስ ልቦናቸውን ሰውነታቸውን በሃጥያት ያሳደፉ ሰዎች ሊቀበሉት የማይገባቸው መለኮት የተዋሃደው እውነተኛ ቁርባን ነው: ሐተታ:- ማን ይከለክላቸዋል ቢሉ ራሳቸው ፈርደው ይከለከላሉና አንድም ቄሱ ይከለክላቸዋልና አንድም እግዚአብሔር በምልዓት በልቡናቸው አድረው ይከለክላቸዋልና: ህዝቡ ያልበቁ ልዑካኑ የበቁ የሆኑ እንደሆነ የህዝቡን ለልዑካኑ ይደርብላቸዋል: ልዑካኑ ያልበቁ ህዝቡ የበቁ ይሆኑ እንደሆነ የልዑካኑን ለህዝቡ ይደርብላቸዋል ህዝቡም ልዑካኑም ያልበቁም የሆኑ እንደሆነ መልአክ ወስዶ በበርረሃ ለወደቁ ባህታውያን ያቀብላቸዋል: ምግብ ሁኑአቸው የሚኖር ቅሉ ይህ ነው: ያም አያውቅም ይህም አያውቅም ያ እንዳይታበይ ይህ ከቀቢጸ ተስፋ እንዳይደርስ ነው::
አኮ ከመ መስዋእቶሙ ለቀደምት አበው ዘበደመ በግዕ ሐርጌ ወላህም:: በደመ በግዕ በደመ ላህም የቀደሙ ሰዎች ይሰውት እንደነበረ መስዋእት አይደለም: አንድም የቀደሙ ሰዎች በደመ ላህም በደመ በግዕ ይሰዉት እንደነበረ መስዋዕት አይደለም: ሐተታ:-ሃርጌን ለበግ የቀጸሉ እንደሆነ ሙክት በላህም የቀጸሉ እንደሆነ ጊድር ማለት ነው::
7:- አላ እሳት ውዕቱ:: መለኮት የተዋሃደው ቁርባን ነው እንጂ እሳት መለኮት የተዋሃደው ቁርባን ነው እንጂ:እሳት ማህየዊ ለርቱአነ ልብ ለዕለ ይገብሩ ፈቃዶ:: ለና ለ አንድ ወገን እሳትም ብዬ ብላችሁ አንድነቱን ሶስትነቱን አውቀው ህማሙን ሞቱን አምነው ሃጥያታቸውን ለመምህረ ንስሓ ነግረው መምህረ ንስሃ ያዘዘውን ሰርተው በሚገባ ለሚቀበሉ ሰዎች የሚያድን እሳት ነው::ሐተታ:- እሳት በመጠን የሞቁት እንደሆነ የበሉት የጠጡትን ያስማማል: ደዌ ይከፍላል: ይህም ከሃጥያት ነጽቶ ቢቀበሉት ይህወተ ስጋ ህይወተ ነፍስ ይሆናል: ደዌ ነፍስ ያርቃልና::
እሳት በላዒ ለአማጽያን ለእለ ይክህዱ ስሞ:: ለና ለ አንድ ወገን ነው እሳት ማህየዊም ብላችሁ ስመ አምላክነቱን ለሚክዱ ሰዎች የሚያቃጥል እሳት ነው:: ሐተታ:- ስመ አምላክነቱን ከካዱ የማን ስጋ የማን ደም ብለው ይቀበሉታል ቢሉ ስመ ቁርባንነቱን ለሚክዱ ሰዎች:: ሐተታ:- ስመ ቁርባንነቱንስ ከካዱ ምን ይረባናል ምን ይጠቅመናል ብለው ይቀበሉታል ቢሉ በግብሩ መካድ አለና::ከሃጥያት ሳይነጹ ቢቀበሉት በፍዳ ላይ ፍዳ የሚያመጣ ስለሆነ እሳት ነበልባሉ ከወረደው ፍህሙ ከመረተው ቀርበው ያለመጠን ቢሞቁት ያቃጥላል ይህም በማይገባ ቢቀበሉት ፍዳ ያመጣልና:: ወይእዜኒ ዘበልዖ ለዝንቱ ህብስት: ወዘሰትዮ ለዝንቱ ጽዋ እንዘ እይደልዎ ደይኖ ወመቅሰፍቶ በልዓ ለርእሱ መንሱትኬ ነሢአ ሥጋሁ በድፍረት ወተመጥዎ ደሙ ዘእንበለ ሃፍረት እንዘቦ ላዕሌሁ ነውረ ሃጥያት እንዲል::ከዚህም ስጋውን ከእሳተ ባቢሎን ደሙን ከማየ ግብጽ ምሳሌ አምጥተው ይናገራሉ: እሳተ ባቢሎን ሰልስቱ ደቂቅን ሳይነካ በአፍአ ያሉ የባቢሎንን ሰዎች አቃጥሎአቸዋል ስጋውም ከሃጥያት ነጽተው የሚቀበሉትን ያድናቸዋል ከሃጥያት ሳይነጹ የሚቀበሉትን ያጠፋቸዋልና ማየ ግብጽ በግብጻውያን ሲለወጥባቸው በእስራኤል አልተለወጠባቸውም ደሙም ከሃጥያት ነጽተው የሚቀበሉትን ያድናቸዋል ከሃጥያት ሳይነጹ የሚቀበሉትን ያጠፋቸዋልና ዛሬም ቀሳውስት ይህን ምሳሌ ይዘው የበደላችሁትን ሳትክሱ የቀማችሁትን ሳትመልሱ ከሃጡያት ሳትነጹ ሳትበቁ ብትቀበሉት ሥጋው ደሙ በነፍስ በስጋ ያስፈርድባችኋል እያሉ አዋጅ ይነግሩበታል::
8:-በአማን እሳት ውዕቱ ዘኢይክሉ ለኪፎቶ እሳታውያን እለ ነደ እሳት እሙንቱ ኪሩቤል ወሱራፌል ከእሳት ከነፋስ የተፈጠሩ ኪሩቤል ሱራፌል ሊይዙት የማይቻላቸው መለኮት የተዋሃደው እውነተኛ ቁርባን ነው ተፈጥሮዋቸው ከእሳት ከነፋስ ነውና:: ወሶበ ኢያእኮትኮ ለዘፈጠርከ እምነፋስ ወነድ ፈጠረ ህየንቴከ ሰንአ ዘማሬ እማይ ወእመሬት እንዲል:: ሐተታ:- ከእለተ ሰሉስ አስቀድሞስ ግብር እም ግብር የተፈጠረ ፍጥረት የለም: የመላእክትም ተፈጥሮ እምሃበ አልቦ ነው: ግብራቸውን ሲያይ እሳት ነፋስ ሃያላን ረቂቃን ፈጣኖች ፈጻሚያነ ፈቃድ ናቸው: መላእክትም ሃያላን ረቂቃን ናቸውና: ለተልኮ ይፋጠናሉና: የፈጣሪያቸውን ፈቃድ ይፈጽማሉና::ሐተታ:- እሳት ሰብዓ ሰዶምን ደቂቀ ቆሬን አጥፍቷል ነፋስም ብእሲት ዘማን ጥቅመ ሰናኦርን ሃራ ጰራግሞንን አጥፍቷልና አንድም የባለሟልነት ስማቸው ነው: እገሌ ነደ እሳት ባለሟል ነው እንዲሉ:: ታሪክ:- ዘኢይክሉ ለኪፎቶ አለ ንጉሱ ዖዝያን ሊቀ ካህናቱ አዛርያስ ይባላል በቀኙ ይቀመጣል: ምነው በቀኜ ትቀመጥብኛለህ ይለዋል ወካህን ይነብር በየማነ ንጉሥ እንጂ ይለኛል ይለዋል:: ከልብሰ መግስቱ ልብሰ ክህነቱ ይበልጣል ምነው ከኔ የበለጠ ልብስ ትለብሳለህ ይለዋል ካህናቲከ ይለብሱ ጽድቀ እንጂ ይለኛል ይለዋል:: ፍርዱን ይገስበታል ምነው ፍርዴን ትገስብኛል ይለዋል እምነ መንግስት የአቢ ክህነት እንጂ ይለኛል ይለዋል አድርጎ ቤተ መንግስትም እያረካከሰ ቤተ ክህነትን እያነጋገሰ እየጠቃቀሰ ቢያውከው በዚያም በዚያም ቢሉ ቀንቶበት ከቤተ መንግስትማ ቤተ ክህነት ከበለጠ እኔስ ባባቴ ከቤተ መንግስት ብወለድ በናቴ ከቤተ ክህነት እውለድ የለምን ብሎ ማእጠንተ ወርቁን ይዞ ልብሰ ተክህኖውን ለብሶ ሊያጥን ገባ: ሲያጥን ጢሱ ቢያርፍበት ከግንባሩ ለምጽ ተቀረጸበት በሻሽ ሸፈነው: ከሻሹ ላይ ወጣበት ለምጻሙን በእስራኤል ስንኳንስ በቤተ መቅደስ በከተማ አያኖሩትምና: እሱን አውጥተው ልጁን አንግሰዋል በዘመኑ የነበረ ነቢይ ኢሣያስ ነው ፈርቶ ሳይገስጸው ቢቀር ለምጽ ወቶበት ሃብተ ትንቢት ተነስቶት 3 አመት ከመንፈቅ ያህል ኖሯል ወእምዝ በዓመተ ሞተ ዖዝያን ንጉስ ርኢክዎ ለእግዚአብሔር እንዘ ይነብር ዲበ መንበሩ ብሩህ ወነዋህ እንዲል: ዖዚያን በሞተበት ወራት ጌታ በመንበረ ጸባኦት እንዳለ ሆኖ ለኢሳያስ ታየው ያ ታፍረው ታከብረው የነበረው ንጉስ ሞተ አልፈ እኔ ግን እልፈት ውላጤ የለብኝም ሲል ሊያድነው ቢሻ መነ እፌኑ ሃበ ህዝብየ እስራኤል ሁሉ ራሱ ጠበቀ አንገቱን ቀበረ ወደወገኖቼ ወደ እስራኤል በመምህርነት ማንን ልስደድ አለ:: እስመ ማዕከለ ህዝብ ዘርኩስ ከናፍሪሆሙ ሃሎኩ አነ እስራኤል ለምጽ ይጸየፋሉ: ደግሞም ትንቢት ተነስቶብኛል እንጂ እኔ አልፈራም ነበር አለው: ወተፈነወ አሃዱ እምሱራፌል ወነስአ ፍህመ በጉጠት ወአልከፎ ከናፍሪሁ ወይቤ አእተትኩ ለከ ሃጥያተከ እንዲል መልአኩን ከአለመ መላእክት ፍህሙን በጉጠት ወስደህ አጉርሰው አለው:: ሃጥያተከ ቢል ለምጹን አራቅሁልህ ሃጥያትከ ቢል ትንቢቱን መለስኩልህ ሲል ነው::
ከዚህ በኋላ ለምጹ ድኖለት ትንቢቱ ተመልሶለት እንደገና አስተምሯልና: ይህም ምሳሌ ነው መልአኩ የቀሳውስት ጉጠት የስልጣነ እግዚአብሄር እሳያስ የምእመናን ለምጽ የፍዳ የመርገም ፍህም የስጋ ወደሙ :: አንድም ከናፍረ ኢሳያስ የምእመናን መልአኩ የዲያቆን ጉጠት የእርፈ መስቀል ፍህም የደሙ ምሳሌ:: መላእክት ስጋውን ደሙን የሚይዙበት ስልጣን የላቸውምና: ዘኢይክሉ አለ: ዘኢተገብረ ለመላእክት ተገብረ ለካህናት የሚያሰኘው ቅሉ ይሄ ነው: አባ መቃርዮስ እንዳየው ስለ ንጽህናው መልአኩ የቄሱን እጅ ይዞ ለማርቆስ ዘዮናኒ ግብጻዊ ሲያቀብለው አይቷል::
9:-ኦ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዓብየኪ: ኦ ቃለ አክብሮ ቃለ አህስሮ ቃለ አራህርሆ ይሆናል: ቃል አክብሮ ኦ ድንግል ምልእተ ውዳሴ ብሎ የሚያመጣው ነው: ቃለ አራህርሆ ኦ ዮሴፍ ወልደ ዳዊት ቃለ አህስሮ ኦ ሃናንያ ኦ አብዳን ሰብአ ገላትያ ነው:: በእንተዝ ያለፈውን አጠፈ እንደገና ብሎ መጽሃፍ ያለፈውንም የሚመጣውንም ማጠፍ ልማድ ነውና የሚመጣውን አጠፈ እመቤታችን ሆይ እናከብርሻለን እናገንሻለን:: ሐተታ:- እኛ እሷን የምናከብራት የምናገናት ሆነን አይደለም ክብርሽን ገናንነትሽን እንናገራለን ሲል ነው::
እስመ ወልድኪ ለነ መብልዓ ጽድቅ ዘበአማን ወስቴ ህይወት ዘበአማን:: እውነተኛውን ምግብ እውነተኛውን መጠጥ አስገኝተሽልናልና ስላስገኘሽልን:: ሐተታ:- ዘበአማን አለ ከመስዋዕተ ኦሪት ሲለይ ያ ስጋዊ ይህ መንፈሳዊ ያ አፍአዊ ይህ ውሳጣዊ ያ ምድራዊ ይህ ሰማያዊ ነውና:: አንድም የዚህ አለም ምግብ ጥዋት በልቶ ለማታ ማታ በልቶ ለጠዋት ያሻል ይህ ግን በሚገባ ከተቀበሉት በሃጥያት ካላሳደፉት ህማሙን ሞቱን ለማዘከር ነው እንጂአንድ ግዜ ከተቀበሉት በሌላ ግዜ አያሻምና:: አንድም የዚህ አለም ምግብ ሃሰር ይሆንል ይለወጥል በሱ ግን ይህ ሁሉ የለበትምና አንድም የዚህ አለም ምግብ ሞትን ያስከትላል ይህ ግን የዘላለም ህይወት ይሆናል አንድም ከማናዊት እመቤታችን ስለተገኘ መብልአ ጽድቅ ዘበአማን ውስቴ ህይወት ዘበአማን አለ:: ይቆየን .......ቸር ያቆየን!!!!!!

Friday, August 6, 2010

ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ክፍል 1

1:- አኮቴተ ቁርባን ዘእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ዘደርሰ በመንፈስቅዱስ አባ ሕርያቆስ ኤጲስ ቆጶስ ዘሃገረ ብህንሳ ጸሎታ ወበረከታ የሃሉ ምስለ ኩሎሙ ህዝበ ክርስቲያን ለዓለመ ዓለም አሜን ::
ሕርያቆስ ማለት ህሩይ ማለት ነው : ለሹመት መርጠውታልና: አንድም ረቂቅ ማለት ነው ምሥጢረ ሥላሴን ይናገራልና : ከሊቃውንትስ ምሥጢረ ሥልሴን የማይናገር የለም ብሎ ከሁሉ ይልቅ እሱ አምልቶ አስፍቶ አጉልቶ ይናገራልና አንድም ፀሐይ ማለት ነው: አብ ፀሐይ ወልድ ፀሐይ መንፈስቅዱስ ፀሐይ ብሎ ጽፏልና : አንድም ብርሃን ማለት ነው: የምዕመናንን ልቦና በትምህርቱ ብሩህ ያደርጋልና : ዘአብርሃ መንበረ ማርቆስ በብርሃን እንዲል :አንድም ንብ ማለት ነው: ንብ የማይቀምሰው አበባ የለመ እሱም የማይጠቅሰው ሊቅ የለም:ይህም እንደምን ነው ቢሉ:ሐዋርያት የተማረ ግብረ ገብ ይሾም ብለው ሥራት ሰርተዋል: ይህስ አይደለም ሁለቱን አስተባብሮ የያዘ አይገኝም ብሎ የተማረ ከሆነ ይሾም ብለዋል::በትምህርቱ መናፍቃንን ተከራክሮ ይመልሳልና ብለው ግብረ ገብም ከሆነ ይሾም ብለዋል:በጸሎቱ ይጠብቃል: በትሩፋቱ ያጸድቃል:ትምህርቱን ውሎ አድሮ ያደርገዋልና ብለው ሾሙት :ይህም አባ ህርያቆስ ያልተማረ ግብረ ገብ ነው :ቢማርም ለጸሎት ለቅዳሴ ያህል ነበር:በብህንሳ በ10000 መነኮሳት በ10000 መነኮሳይያት ተሹሟል በብዙም መሾም ልማድ ነው::
አባ ሆርና አባ ኤስድሮስ በ1000 አባ አሞን በ3000 አባ ጳኩሚስ በ6000 አባ ሰራብዮን በ10000 ተሾሙ:ይህችም ብህንሳ ቅድመ ትሰይም አርጋድያ ወድህረ መኑፍ ይላል: ብዙ ግዜ ስመ ተፋልሶ አግኝቷታል :በፊት አርጋድያ ኋላም መኑፍ ተብላለች ዛሬም ብህንሳ ትባላለች:ሴትና ወንድ ያልተለየባት ገዳም ናት:እንደ ዘጌ እንደ ቆራጣ እንደ ቀንጠፋሜ እርሱም ግብረ ገብ ነውና ሥራት ቢያጸናባቸው ይጣሉታል:ያልተማረ ነውና ይንቁታል: ከመጠምጠም መማር ይቅደም እንዲሉ ከመሾም መማር አይቀድምምን እያሉ; እሱ ግን ወእቀውም ዮም በትህትና ወበፍቅር ብሎ እንዲያመጣው: እንደጠሉኝ ልጥላቸው እንደ ናቁኝ ልናቃቸው ሳይል በፍቅር እና በትህትና ጸንቶ ያስተምራቸው ነበር::
ከዕለታት ባንዳቸው በምን ምክንያት እንሻረው አሉ:ቀድሰህ አቁርበን ብለን በዚህ ምክንያት እንሻረው ብለው መክረው ቀድሰህ አቁርበን አሉት: የሱ ግን ተምኔቱ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም የእመቤቴ ምስጋና እንደባህር አሸዋ እንደ ሰማይ ኮከብ በዝቶልኝ እንደምግብ ተመግበው እንደ መጠጥ ጠጥቼው እንደ ልብስ ለብሼው እያለ ይመኝ ነበር:ቅዳሴ ገብቶ ሥርዓቱን ጨርሶ ከፍሬ ቅዳሴው ሲደርስ ከሊቃውንት ቅዳሴ የሚያስቸግር የማንን እናውጣለት እያሉ ሲያወጡ ሲያወርዱ የለመኗትን የማትነሳ የነገሯትን የማትረሳ እመቤት ገልጻለት ጐሥዓ ልብየ ቃለ ሠናየ ብሎ ወይእዜኒ ንሰብሐ እስኪል ድረስ ሰተት አድርጎ ተናግሮታል: የሚንቁት የሚጠሉት ይህ የነገሩትን ቀለም እንኳን አከናውኖ መናገር የማይችል ዛሬስ እንግዳ ድርሰት እደርሳለው ብሎ አገኝ አጣውን የቆጥ የባጡን ይቀባጥራል: ብለው አደነቁበት የሚወዱት የሚያከብሩት ከመንፈስቅዱስ ነው እንጂ እንዲ ያለ ምሥጢር ከእሩቅ ብዕሲ ይገኛልን ብለው አደነቁለት: ወዲያው የሚወዱት የሚያከብሩት ጽፈን ደጉሰን አንይዘውምን አሉ: የሚንቁት የሚጠሉት ደግሞ ማን ተናገረው ብለን እንይዘዋለን አሉ እንደ ሊማዱ አድርገን አንይዘውም አሉ:: ለሃገራቸው እንግዳ ድርሰት የተደረሰ እንደሆነ ጽፈው ደጉሰው ከእሳት ይጥሉታል: ከእሳት ደህና የወጣ እንደሆነ ከውሃ ይጥሉታል ከውሃ የወጣ እንደሆነ ከህሙም ላይ ይጥሉታል ድውይ የፈወሰ እንደሆነ ደገኛ ድርሰት ነው ብለው ይይዙታል::
ይህንንም ቅዳሴ ማርያም ጽፈው ደጉሰው ከእሳት ላይ ጣሉት ከእሳት ደህና ወጣ: ከውሃ ጣሉት ከውሃ ደህና ወጣ: ከህሙም ላይ ጣሉት ድውይ ፈወሰ: ይልቁንም ሙት አስነስቷል:: ደገኛ ድርሰት ነው ብለው ጽፈው ደጉሰው ይዘውታል:በጥራዝም 14ኛ አድርገው ጠርዘውታል: ከ14ቱ ቅዳሴም ተአምራት ያልተደረገበት የለም: የቀደሰበት ምን ቀን ነው ቢሉ: ከእመቤታችን ከ 33ቱ በዓላት ባንዱ ቀን ነው: አንድ ባህታዊ ከባለሟልነት የተነሳ ከ33ቱ በዓላት ማንን ትወጃለሽ ብሎ እመቤታችንን ጠየቃት:ኪዳነምህረትን ልደታን አስተርአዮን ፍልሰታን አለችው: ከሊህ ከ4ቱስ ማንን ትወጃለሽ ቢላት ከጸባብ ወደ ሰፊ: ከጨለማ ወደ ብርሃን: የወጣውበት ነውና ልደቴን እወዳለው አለችው: ቀድሞ እነ ሳልወለድ እናትና አባቴን መባችሁን አንቀበልም ብለው አዝነው ተክዘው ነበር: የነሱ ሃዘን ሃዘኔ ነውና እነን ከወለዱ በኋላ መባቸውን ተቀብለዋቸው ደስ ብሎዋቸዋል: የነሱ ደስታ ደስታዬ ነውና እንዳለችው የልደታ እለት ነው የቀደሰው:: እሱስ ማንን ሊቀድስ ኖሯል ቢሉ ከቅዳሴ ሐዋርያት ሌላ አያቅም ነበርና ቅዳሴ ሐዋርያትን: ይህስ አይደለም ለእመቤታችን ቅዳሴ ሐዋርያት ምኗ ነው: ምን ቢቸግር ተበድሮ ጋሬዳ እንዲሉ ቅዳሴ እግዚእን ሊቀድስ ነበር ስሟን ባያነሳ እምድንግል ተወሊዶ ከመ ፈቃድከ ይፈጽም ብሎ በምሥጢር ያነሳታል::
ከባህር ወዲህስ ማን አምጥቶልናል ቢሉቅዱስ ያሬድ ማይ ኪራህ መደባይ ታብር በሚባል ቦታ ይኖር ነበር እመቤታችን ቅዱስ ኤፍሬምን ከሶርያ አባ ሕርያቆስን ከብህንሳ በደመና ጠቅሳ ያረድ ካለበት አድርሳ አንተ ውዳሴየን አንተ ቅዳሴየን ነግራችሁት በዜማ ያድርስ ብላቸው እነሱም ነግረውት በዜማ አድርሶታል:: ከዚሁ አያይዞ 13ቱንም ቅዳሴ በዜማ ደርሷል: ይህም ሊታወቅ ሥረይ በቅዳሴ ማርያም ይበዛል::ከተከዜስ ወዲህ ማን አምጥቶልናል ቢሉ ሳሙኤል ትውልደ ጌዴዎን ዘገበዘ አክሱም ይለዋል እሱ አምጥቶልናል እሱም ይሄን እየደገመ ሲሄድ ክንድ ከስንዝር ከመረት መጥቆ ይሄድ ነበር: ከዕለታትም በአንዳቸው ውሃውን ቢባርከው ህብስት ሆኖለት ተመግቦ ምዕመናንን መግቧቸዋል:: እመቤታችንም የፍቅር ምልክት ሁለት ንዋያት ሰታዋለች ነጭ እጣን እና እንቁ ነው: ከዛም አያይዛ ውዳሴየን ከቅዳሴዬ ጋራ አንድ አድርጎ የሚደግመውን ሰው አንተ ከገባህበት ውሳጤ መንጦላዕት አገባዋለው:ብላ ተስፋውን ነግራዋለች:: ይሀውም ሊታወቅ ዛሬ በዋልድባ ያጠና በቃሉ: ያላጠና በመጽሃፍ ቅዳሴ ማርያም ሳይደግም የሚውል የለም:ይህም ተስፋ ውዳሴዋን ከቅዳሴዋ ጋር አንድ አድርጎ ለምደግም ሰው ሁሉ ነው:እንጂ ለሱ ብቻ አይደለም:ዳንድ ባህታዊ ከምስጋናሽ ሁሉ ማንን ትወጃለሽ ብሎ ቢጠይቃት ልጄ ዳዊትን አቡነ ዘበሰማያትን ቢደግሙለት እንዲወድ እኔም ውዳሴዬን ቅዳሴዬን ቢደግሙልኝ ወዳለው ብላዋለች ::
አባ ሕርያቆስ ተሹሞ ሳለ ብዙ ድርሳንን ደርሷል ብዙ ተግሳጽ ጽፏል ከብዙውም አንዱ ይህ ቅዳሴ ነው እረፍቱ በጥቅምት 2 ነው::
ልመናዋ ክብሯ በኛ ይደርብንና ህብስቱን በጻህል ወይኑን በጽዋ አድርጎ አክብሮ ለውጦ ሥጋ ወልደ እግዚአብሔር ደመ ወለደ እግዚአብሔር በሚያደርግበት ግዜ በብህንሳ ኤጲስ ቆጶስ የተሾመ አባ ሕርያቆስ በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾለት እመቤታችንን ያመሰገነበት ምስጋና ይህ ነው:: ቁርባን ቀሳውስት ሥጋውን በጻህል ወይኑን በጽዋ አድርገው ወደ መንበር የሚያቀርቡበት አኰተት የሚለውጡት የሚያከብሩት አንድም በክብር በባለሟልነት ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርቡ አንድም ቁርባን የሚቀበሉት የሚያቀብሉት አኰተት የሚለውጡት የሚያከብሩት ልመናው ክብሩ በኛ ይደርብንና በብህንሳ ኤጲስ ቆጶስ የተሾመ አባ ሕርያቆስ በመንፈስቅዱስ ተገልጾለት የተናገረው ቅዳሴ ይህ ነው: ጸሎታ ወበረከታ ቢል ተመስጋኝቱን ሲያይ: ክብሯ ልመናዋ ይደርብንና ጸሎቱ ወበረከቱ ቢል አመስጋኙን ሲያይ ነው::
2:- ይ:ካ: እግዚአብሔር ምስለ ኰልክሙ ቄሱ:-እግዚአብሄር በሁላችሁም አድሮባችሁ ይኑር ይበል::
ይ:ሕ: ምስለ መንፈስከ ህዝቡም እንደቃልህ ይደረግልን ይበሉ::
ይ:ካ: አእኩትዎ ለአምላክነ :-ቄሱ ፈጣርያችንን አመስግኑት ይበል
ይ:ሕ: ርቱዕ ይደሉ :- ህዝቡም ዕውነት ነው ይገባል ይበሉ
ይ:ካ: ብነ ሃበ እግዚአብሔር አምላክነ
ህዝቡም በፈጣርያችን በእግዚአብሄር ዘንድ ዋጋ አለን ይበሉ::
3:- መጽሃፍ ከመጽሃፍ ማያያዝ ልማድ ነው: አባቷ ዳዊት ለንጉሰ ሰማይ ወምድር ምስጋና ላቅርብ ባለ ግዜ ጐሥዐ ብሎ ተናግሮ ነበርና እሱም ለንግስተ ሰማይ ወምድር ምስጋና ላቅርብ ባለ ግዜ ጐሥዐ አለ አንድም ለአባቷ ለዳዊት የገለጸ መንፈስቅዱስ ምሥጢር ከምስጢር አያይዞለት ጐሥዐ አለ ወአየድዕ ይላል በልብ መደብ ቁሞ ወአነ አየድዕ ይላል በቃለ መደብ ቁሞ ልቦናዬ በጎ ነገርን አውጥቶ ተናገረ::አንድም ልቦናየ ስንቡል መንፈስቅዱስን ተቀብሎ በጎ ነገርን ገሳ ሐተታ:-በሃገራቸው የተመገቡት ምግብ ያልተስማማቸው እንደሆነ ዑድ ሰንደል የሚባል ሽቱ አለ ያንን ተመግበው በጎ በጎ ነገር ገሣው ይላሉና ያጎሥዓኒ እንዲል ትግሬ ሐተታ:- ሶስት ግዜ ጐሥዐ ጐሥዐ ጐሥዐ ብሎ መላልሶ ተናገረ ስለምን ቢሉ በንጽሃ ስጋ በንጽሃ ነፍስ በንጽሃ ልቦና መዓረግ አምሳል አንድም ወጣንያን ማዕከላውያንን ፍጹማን የሚያመሰግኗት ስለሆነ: አንድም በዚህ አለም በገነት በመንግስሠማያት ያሉ ጻድቃንየሚያመሰግኗት ስለሆነ: ከዚህስ አስቀድሞ መንግስተ ሰማይ የገባ የለም ብሎ ኋላ መንግስተ ሰማያት የሚገቡ ጻድቃን የሚያመሰግኗት ሲለሆነ: አንድም ሊቃውንት በሚስጥረ ሥላሴ መጀመር ልማዳቸው ነው: ሦስት ግዜ ደጋግሞ መናገሩ የሦስትነት: ቃሉ አለመለወጡ የአንድነት:ምሳሌ ነው:አንድም ወአነ አየድዕ ቅዳሴሃ ወአነ አየድዕ ውዳሴሃ ወአነ አየድዕ ዕበያቲሃ የሚል ነውና ሦስት አርዕስት ተናገረ ለሦስቱም ያመጣል::
4:-ወአነ አየድዕ ቅዳሴሃ ለማርያም:- አባቷ ዳዊት ወአነ አየድዕ ግብርየ ለንጉሥ ብሎ ነበርና ለዚያ ዋዌ እኔም የእመቤታችንን ምስጋና እናገራለው አለ ሐተታ:- መጀመርያ ጐሥዐ ብሎ ነበርና ለዚያ ህዳግ ይህስ ለራሱ አርእስት ነው ብሎ አለ በቅድስና ወበንጽህና ስርጉት አንቲ የሚል ነውና ለዚያ አርዕስት ነው::
አኮ በአብዝኖ በማብዛት አይደለም : አላ በአውህዶ በማሳነስ ነው እንጂ ሐተታ:-የእመቤታችን ምስጋና ከምስጋና ቢበዛ እንጂ ያንሳልን? መትህተ ፈጣሪ መልዕልተ ፍጡራን አይደለችምን ቢሉ እውነት ነው የእመቤታችን ምስጋና ሰማይና ምድር ብራና አብህርት ቀለም ዕጽው ብርዕ አዕባን መድመድ: መላዕክት ደቂቀ አዳም ጸሃፍት ቢሆኑ ባልተፈጸመም ነበር:እንደቅድስናዋ እንደንጽህናዋ አይደለም ሲል እንዲህ አለ ከዚያ ሁሉ ቅዱስ ቄርሎስ የቴዎዶስዮስን እህቶች የአርቃድያ የመሪናን ምስጋናቸውን ተናግሮ ዝውዳሴንዘተናገርነ ይውህደ እምክብርክን እንዳለ አንድም ንባብን በማብዛት ምሥጢሩን በማሳነስ አይደለም: ንባቡን በማሳነስ ምሥጢሩን በማብዛት ነው እንጂ::
ወአነ አይድዕ ውዳሴሃ ለድንግል:- እኔም የእመቤታችንን ምስጋና እናገራለው ሐተታ:-ሁለተኛ ጐሥዐ ብሎ ነበርና ለዚያ ህዳግ ይህስ ለራሱ አርእስት ነው ብሎ ኦ ድንግል አኮ ስፋጣን ዘናዘዙኪ አላ መላእክተ ሰማይ ሐወጹኪ በከመ ተብህለ ካህናት ወሊቃነ ካህናት ወደሱኪ የሚል ነውና::
አኮ በአንሆ በቃለ ዝንጋዔ:- ዝንጋዔን የሚያመጣ ዝንጋዔን የሚያስከትል ነገርን በማብዛት አይደለም: ብዙ ቢያወጉ ይዘነጉ: ብዙ ቢተቹ ይሰለቹ:እንዲሉ ነገር ከበዛ ዘንድ ከምን ተነስቶ ከዚህ ደረሰ ይባላልና ነው::
አላ በአሕፅሮ:-በማሳጠር በመጠቅለል ነው እንጂ ሲሰበር ይሰንጠር ሲረዝም ይጠር እንዲሉ:
ወአነ አየድዕ ዕበያቲሃ ለድንግል:- የድንልን ገናንነቷን እናገራለው ሐተታ:- ሦስተኛ ጐሥዐ ብሎ ነበርና ለዚያ ህዳግ ይህስ ለራሱ አርእስት ነው ብሎ ኦ ማርያም ናፈቅረኪ ወናዓብየኪ ብሎ የሚያመጣ ነውና: ይህስ አይደለም አርዕስት ተቀዳደመ ለፊተኛው አርቆ ለኋለኛው አቅርቦ አይሰጥም ብሎ መጽአ ሃቤኪ ቃል ብሎ የሚያመጣ ነውና:: ወአነ አየድዕ ውዳሴሃ : ወአነ አይድዕ ቅዳሴሃ : ወአነ አይድዕ ዕበያቲሃ ብሎ ሦስት ጊዜ መላልዞ ተናገረ::
ኦ ማርያም በእንትዝ ናፈቅረኪ ወናዓብየኪ ኦ ድንግል ምልዕተ ውዳሴ: ኦ ድንግል አኮ ዘተአምሪ ርስሃተ የሚል ነውና: አንድም አባቷ ዳዊት ቀደሰ ማህደሮ ልዕል:መሰረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን እስመ ሓረያ እግዚአብሄር ለጽዮን ብሎ ሦስት ግዜ መላልሶ አመስግኗታል:: ይቆየን የዚህ ክፍል ሁለት ነገ ይቀጥላል ..............ችቸር ያቆየን!!!!!

ውዳሴ ማርያም አንድምታ ዘቀዳም :- ክፍል 1

ውዳሴሃ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ዘይትነበብ በዕለተ ቀዳሚት ሰንበት
በክብር ትቀድማለችና:: አንድም በዕለተ ሰንበት አይሁድ የሚል አብነት ይገኛል አይሁድ በብሉይ የሚያከብሯት ሲል ነው :: በዚህም ቀን እመቤታችን ትመጣለች :: የብርሃን ድባብ ይዘረጋል የብርሃን ምንጣፍ ይነጠፋል :: ከዚያ ላይ ሁና ሰላም ለከ ኦፍቁርየ ኤፍሬም ትለዋለች :: እርሱም ታጥቆ እጅ ነስቶ ይቆማል:: ወድሰኒ ትለዋለች ክርክር አልቋልና :: ባርክኒ ይላታል :: በረከተ ወልድየ ወአቡሁ ወመንፈስቅዱስ ይህድር በላዕሌከ ትለዋለች :: ተባርኮ ምስጋናዋን ይጀምራል ::ውዳሴ ዘቀዳሚት ዉዳሴ በቀዳሚት ዉዳሴሃ ለእግዝትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ዘይትነበብ በዕለተ ቀዳሚት ሰንበት ይላል ቃለ ጸሐፊ ነው :: እርሱ ግን ንጽህት ወብርህት ብሎ ይጀምራል ::
" ንጽህት ወብርህት"
ንጽህት ነሽ ብርህት ነሽ ::
" ወቅድስት በኩሉ::"
በአፍኣ በውስጥ ንጽህት ነሽ : እርሷ የምትለወጥ ሁና አይደለም : እርሱ እየቀደመ እየበቃ ማየቱን መናገር ነው ::
" እንተ ሐቀፈቶ ለእግዚእ በእራሃ :"
ጌታን በማሃል እጅሽ የያዝሺው : ህጻናትን አናት ይወርድላቸዋልና ብለው በማሃል እጃቸው እንዲይዟቸው :: አንድም በክንድሽ የያዝሽው ::
" ወኩሉ ፍጥረት ይትፌሥሑ ምስሌሃ "
ፍጥረት ሁሉ ካንቺ ጋር እንዳንቺ ደስ ይላቸዋል :: እንዘ ይጸርሁ ወይበሉ
" ሰአሊ ለነ ቅድስት "
እያሉ አንድም ተፈስሒ ኦ ምልዕተ ጸጋ ::ምልዕተ ክብር ሆይ ( ተፈሥሒ) ደስ ይበልሽ እያሉ ::
" ተፈሥሒ እስመ ረከብኪ ሞገር ተፈሥሒ እግዚአብሔር ምስሌኪ :"
እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነስቶ ካንቺ ጋር አንድ ባህርይ ቢሆን ባለሟልነትን አግኝተሻልና ( ተፈሥሒ) ደስ ይበልሽ ::
" ናስተበፅዕ ዕበየኪ ኦ ግርምት ድንግል "
ግርምት ድንግል ክብርሺን ገናንነትሽን ዕፁብ ዕፁብ እያልን እናመሰግናለን :: ግርምትነትቷ በአይሁድ በመናፍቃን በአጋንንት ዘንድ ነው ::
" ወንፌኑ ለኪ ፍሥሐ ምስለ ገብርኤል መልአክ :"
ከመልአኩ ጋራ እንደ መልአኩ ምስጋና እናቀርባለን :: ምስጋናውን ፍስሐ አለው : ተፈሥሒ ተፈሥሒ እያለ ነውና ::
" እስመ እምፍሬ ከርሥኪ ኮነ መድሃኒተ ዘመድነ :"
ከማህፀንሽ ፍሬ የባህሪያችን ድህነት ተገኝቷልና አንድም የማህፀንሽ ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስ የባህሪያችን ድህነት ሆኗልና ::
" ወአቅረበነ ሃበ እግዚአብሔር አቡሁ :"
ከአባቱ ጋራ አስታረቀን " ሰአሊ ለነ ቅድስት "
ካባቱ ጋራ ካስታረቀን ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን ::
" ከመ ከብካብ ዘአልቦ ጥልቀት :"
እንደ ሰርግ ቤት አደፍ ጉድፍ የሌለብሽ ሆነሽ ቢያገኝሽ :
" መንፈስቅዱስ ሃደረ ላዕሌኪ "
መንፈስቅዱስ አድሮብሻልና :
" ወሃይለ ልዑል ጸለለኪ:"
ሃይለ ልዑል ወልድም ሥጋሽን ለብሷልና አንድም መንፈስቅዱስ ከሦስቱ ግብራት ከልክሎሻልና ሃይለ ልዑል ወልድም ከሦስቱ ግብራት ከልሎሻልና
" ኦ ማርያም አማን ወለድኪ ቃለ ወልድ አብ ዘይነብር ለዓለም :"
ለዘላለም ጸንቶ የሚኖር አካላዊ ቃልን ወለድሽልን :
"መጽአ ወአድሃነነ እምሃጢያት:"
ሰው ሆኖ ከሃጢያት አዳነን አንድም ከሃጥያታችን ፍዳ ያዳነን " ሰአሊ ለነ ቅድስት "
ሰው ሆኖ ከሃጥያታችን ፍዳ ካዳነን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን ::
" አንቲ ውእቱ ዘመድ ዘእምሥርወ ዳዊት:"
ከዳዊት ሥርው የተገኘሽ ባህርይ አንቺ ነሽ :ሥር ወደላይም ወደታችም ያድጋል ወደላይ ቢሉ ዕሴይ ወደታች ቢሉ ኢያቄም መገናኛው ዳዊት ::
" ወለድኪ ለነ በሥጋ መድሃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ :"
መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋ ወልደሽዋልና :
" ዋህድ ቃል ዘእምአብ ዘእምቅድመ ዓለም ህልው :"
ቅድመ ዓለም የነበረ ከአብ ባህርይ ዘእምባህርይ አካል ዘእምአካል የተወለደ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አካላዊ ቃል :
" ሃብአ ርእሶ :"
ባህርዩን በስጋ ቢሰውር:
" ወነስአ እምኔኪ አርኣያ ገብር :"
ከአንቺ አርአያ ገብርን ቢነሳ መድሃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ወልደሽልናልና : አንድም ቅድመ ዓለም ህቡዕ የሚሆን አካላዊ ቃል ህብዓ ርእሶ ባህርዩን በስጋ ሠወረ :ካንቺም ሃየሰ ወረሰ ከብረ ተለዓለ ነገሠ መባልን ገንዘብ አደረገ : " ሰአሊ ለነ ቅድስት "
ሃየሰ ወረሰ ከብረ ተለዓለ ነገሰ ከሚባል ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን ::
" ኮንኪ ዳግሚተ ሰማይ ዲበ ምድር :"
ከምድር በላይ ያለሽ ሁለተኛ ሰማይ አንቺ ነሽ : አንድም ከምድር በላይ ያለች የጠፈር ባልንጀራ ሆንሽ :
" ኦወላዲተ አምላክ ዘእንበለ ርኩስ:ሠረቀ ለነ እምኔኪ ፀሐየ ጽድቅ:ዘእንበለ ዘርዕ ወኢሙስና : ሰአሊ ለነ ቅድስት :"
አደፍ ጉድፍ ሳይኖርብሽ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ፀሐየ ጽድቅ ጌታ ካንቺ ተወልዷልና ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው እንደተናገሩ : ዘር ምክንያት ሳይሆንሽ መለወጥ ሳያገኝሽ ወልደሽዋልና : ዘር ምክንያት ሳይሆንሽ ከወለድሽው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን ::
"አንቲ ውእቱ ደብተራ እንተ ተሰመይኪ ቅድስተ ቅዱሳን:ወውስቴታ ጽላተ ኪዳን:መሶበ ወርቅ እንተ መና ህቡዕ:ዘውእቱ ወልደ እግዚአብሔር መጽአ ወሃደረ ሃበ ማርያም ድንግል "
ከተለዩ የተለየሽ ከከበሩ የከበርሽ ደብተራ አንቺ ነሽ :ሕግ የተጻፈበት ኪዳን ያለብሽ: መና ያለበት መሶበ ወርቅ ያለብሽ:ይህውም ሰው ሆኖ በማህጸንሽ ያደረው ወልደ እግዚአብሔር ነው : ደብተራ የእመቤታችን ምሳሌ ቅድስት የነፍሷ ምሳሌ ቅዱሳን የ4ቱ ባህርያት ምሳሌ ታቦት የመንፈስቅዱስ ጽላት የልቦናዋ ቃሉ በመንፈስቅዱስ የተገለጸላት ምሥጢር :: አንድም ቅዱሳን የሥጋዋና የነፍሷን : ቅድስት የልቦናዋ : ታቦት የማህጸኗ ጽላት : የትስብእት ቃሉ የመለኮት ምስሌ :
" ተሰብአ እምኔሃ ቃለ አብ : ወወለደቶ ውስተ ዓለም ለንጉሠ ስብሐት : መጽአ ወአድሃነነ :ትትፌሣህ ገነት እመ በግዕ ነባቢ :"
አካላዊ ቃል ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆነ :የክብር ባለቤት እርሱን በዚህ ዓለም ወለደችው : ሰው ሆኖ ያዳነን : የነባቢ በግዕ እናቱ ደስ ይላታል ኢነባብያን አባግዕ አሉና ከዚያ ሲለይ በግዕ ነባቢ አለ : አንድም 7ቱን አጽራሐ መስቀል የተናገረውን ሲል በግዕ ነባቢ አለ :
" ወልደ አብ ዘይነብር ለዓለም : መጽአ ወአድሃነነ እምሃጥያት : ሰአሊ ለነ ቅድስት :"
ለዘላለሙ ጸንቶ የሚኖር አካላዊ ቃል ሰው ሆኖ ከሃጥያት ያዳነን አንድም ከሃጥያታችን ፍዳ ያዳነን :ሰው ሆኖ ከሃጥያታችን ፍዳ ካዳነን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን:: ይቆየን የቅዳሜን ክፍል 2 በሚቀጥለው ሳምንት እንመለስበታለን.............ቸር ያቆየን !!!!!

Tuesday, May 18, 2010

ቅዱስ ያሬድ

በግንቦት 11 ዕለት የሱራፌል አምሳላቸው የሆነ ኢትዮጵያዊው ማህሌታይ ቅዱስ ያሬድ አረፈ::ይህ ቅዱስ ከአባ ጌዴዎን ዘመዶች ወገን እርሱም በኢትዮጵያ አገር ከታነጹት አብያተ ክርስቲያናት ለምትቀድም ከአክሱም ካህናት ውስጥ ነው: እርሷም አስቀድሞ የክብር ባለቤት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት በውስጥዋ የተከበበ እና አምላክን በወለደች በእመቤታችን በከበረች ድንግል ማርያም ስም የከበረች ናት ::
የዚህ ቅዱስ አባት አዳም የእናቱም ስም ታውክሊያ ሲባሉ :በ512 ዓ ም በአክሱም ከተማ ተወለደ:: እናት እና አባቱም ልጃቸውን ለማስተማር ወደ ዘመዳቸው አባ ጌዴዎን ልከው እንዲማር አደረጉት : ይህም አባት አባ ጌዴዎን ትምህርትን ሊያስተምረው በጀመረ ግዜ መቀበልም ማጥናትም ተሳነው እስከ ብዙ ዘመንም መዝሙረ ዳዊትን ሲማር ኖረ ነገር ግን ከልቡ ማጥናትን እምቢ አለው:መምህሩም አብዝቶ ደበደበው ባሳመመውም ግዜ መታገስ ተሳነው ከአባቶቹ ቤትም ወቶ ዕብነ ሃኪም ወደተቀበረበት ገዳም ሄደ : በውስጡም የወርቅ የብር የልብስ መቀመጫዎች የተመሉ ናቸው: ከአንዲትም ዛፍ አጠገብ ደረሰ ከዚያም አረፈ ትልም ወደ ዛፏ ሲወጣ አየ :ወደ ዛፊቱም እኩሌታ ደርሶ ወደ ምድር ይወድቃል :ሁለተኛም ተመልሶ ወደ ላይ ይወጣል መጀመርያ ወደ ደረሰበት ሲደርስ ይወድቃል:ሲወጣ ሲወድቅ ብዙ ግዜ ያደርጋል : ወደ ሌላ ቦታም አይሄድም
ከዚህም በኋላ በብዙ ጥረት በብዙ ትጋት በብዙ ድካም በዚያ ከዛፏ ላይ ወጣ:ከዚያችም ከዛፏ ላይ ተቀምጦ በላ :ቅዱስ ያሬድም ወደዚያ ዛፍ ላይ ይወጣ ዘንድ እንደሚተጋ ብዙ ግዜም ከላይ ሳይደርስ ከመካከል እንደሚወድቅ ከዚያም በኋላ በጭንቅ ወደ አሰበው እንደደረሰ የፈለገውንም እንዳገኘ የትሉን ትጋት ባየ ግዜ ሰውነቱን ግርፋቱን እንደምን አትታገሺም ህማሙንስ እንደምን አትችይም አላት መታገስንስ አብዝተሽ ኖሮ ቢሆን እግዚአብሄር በገለጠልሽ ነበር ይንንም ብሎ አለቀሰ ወደ መምህሩ ወደ ጌዲዮን ተመለሰ አባት ሆይ ይቅር በለን እንደቀድሞ ንገረኝ አስተምረኝም አለው:መምህሩ ጌዲዮንም እንዳልከው ይሁን አለው 150ውን መዝሙረ ዳዊት:መሃልየ ነብያትን :መሃልየ መሃልይን :የእመቤታችን ድንግል ማርያምን ምስጋና ነገረው:81ዱ መጻህፍትን ትርጓሜ የሌሎች መጽሃፍትን ቁትር እና የመሳሰሉትን መጽሃፍተ ሊቃውንት ሁሉ በአንድ ቀን አጥንቶ ፈጸመ::
ከዚህ በኋላ በብዙ ለቅሶ ወደ እግዚአብሄር በለመነ ግዜ ልቡናው ብሩህ ሆኖለት በአጭር ግዜ የብሉይ እና የሃዲስ መጽሃፍትን ተምሮ ፈጸመና ዲቁና ተሾመ:በዚያም ወራት እንደዛሬ በከፍተኛ ቃል የመዝሙር ማህሌት የለም ነበር በትሁት እንጂ :: እግዚአብሄርም መታሰቢያ ሊያቆምለት በወደደ ግዜ ከኤዶም ገነት 3 አእዋፍን ላከለት እነርሱም በሰው አንደበት ተናግረውት ወደ እየሩሳሌም ሰማያዊት ከእነሱ ጋር አወጡት በዚያም 24ቱ ካህናተ ሰማይ የሚያመሰግኑበትን ማህሌት ተማረ::
ወደ አነዋወሩ ወደ ምድርም በተመለሰ ግዜ በአክሱም ዳር ወደ ከበረች ቤተ ክርስቲያን በ3 ሰዓት ገባ በታላቅም ቃል ሃሌ ሉያ ለአብ:ሃሌ ሉያ ለወልድ: ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ :የፅዮንም ደገኛዋ ሰማይን ፈጠረ ዳግመኛም እንዴት እንደሚሰራት የድንኳንን አሰራር ለሙሴ አሳየው አስተማረው አለ:: ይህቺም ምስጋና አርያም ብሎ ጠራት:የቃሉንም ድምጽ በሰሙ ግዜ ንጉሱም ንግስቲቱም ጳጳሱም ከካህናቱ ሁሉ ጋር የመንግስት ታላላቆች እና ህዝቡ ሁሉ ወደ እርሱ ሮጡ:ሲሰሙትም ዋሉ ከዚህም በኋላ ከአመት እስከ አመት በየክፍለ ዘመኑ በክረምት እና በበጋ:በመጸው እና በጸደይ:በአጽዋማት እና በባእላት :በሰንበታትም እንዲሁም በመላእክት በአል በነብያት እና በሃዋርያት በጻድቃን እና በሰማእታት በደናግልም በአል የሚሆን አድርጎ በሶስቱ ዜማው ሰራ :ይህውም ግዕዝ ዕዝል አራራይ ነው::
የሰው ንግግር የአእዋፍ የእንሥሳትና የአራዊት ጩሀት ከነዚህ ከሶስቱ ዜማ አይወጣም :በአንዲት እለትም ቅዱስ ያሬድ ከንጉስ ገበረመስቀል እግር በታች ቆሞ ሲዘምር ንጉሱም የያሬድን ድምጽ እያዳመጠ ልቡ ተመስጦ የብረት ዘንጉን ወይም መቋምያውን በያሬድ እግር ላይ ተከለው ከእርሱም ደምና ውሃ ፈሰሰ ያሬድም መሃሌቱን እስከሚፈጽም አልተሰማውም ነበር ንጉሱም አይቶ ደነገጠ በትሩንም ከእግሩ ላይ ነቀለ ስለፈሰሰው የደምህ ዋጋ የፈለከውን ለምነኝ ብሎ ለያሬድ ተናገረው ያሬድም ላትከለክለኝ ማልልኝ አለው ንጉስም በማለለት ግዜ ወደ ገዳም ሄጄ እመነኩስ ዘንድ አሰናብተኝ አለው ንጉሱም ሰምቶ ከመኳንንቱ ጋር እጅግ አዘነ ተከዘም እንዳይከለክለውም መሃላውን አሰበ እያዘነም አሰናበተው ከዚ በኋላም ቅዱስ ያሬድ ወደ በተክርስቲያን ገብቶ በታቦተ ጽዮን ፊት ቆሞ ፈጽሞ የከበርሽ እና የተመሰገንሽ ከፍ ከፍ ያልሽ የብርሃን መውጫ የህይወት ማዕረግ የሆንሽ የሚለውን ምስጋና (አንቀጸ ብርሃን) እስከመጨረሻ በተናገረ ግዜ ክንድ ያህል ከምድር ከፍ ከፍ አለ::
ከዚህ በኋላ ወደ ሰሜን ሃገር ሄዶ በጾም በጸሎት ተወስኖ ስጋውን እጅግ እያደከመ ኖሮ ገድሉን በዚያ ፈጸመ እግዚአብሄር ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጠው ከዚ በኋላ ግንቦት 11 ቀን በሰሜን ተራራ አሁን ቅዱስ ያሬድ ገዳም ባለበት ቦታ ተሰወረ :የአባታችን የአምሳለ ሱራፌል የሊቁ ማህሌታይ የቅዱስ ያሬድ ጸሎቱ በረከቱ ረድኤቱ በኛ በህዝበ ክርስቲያኑ ላይ በሃገራችን በኢትዮጵያ ላይ ለዘላለም በእውነት ይደርብን !!!!!አሜን..........................ቸር ያቆየን!