Tuesday, May 18, 2010

ቅዱስ ያሬድ

በግንቦት 11 ዕለት የሱራፌል አምሳላቸው የሆነ ኢትዮጵያዊው ማህሌታይ ቅዱስ ያሬድ አረፈ::ይህ ቅዱስ ከአባ ጌዴዎን ዘመዶች ወገን እርሱም በኢትዮጵያ አገር ከታነጹት አብያተ ክርስቲያናት ለምትቀድም ከአክሱም ካህናት ውስጥ ነው: እርሷም አስቀድሞ የክብር ባለቤት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት በውስጥዋ የተከበበ እና አምላክን በወለደች በእመቤታችን በከበረች ድንግል ማርያም ስም የከበረች ናት ::
የዚህ ቅዱስ አባት አዳም የእናቱም ስም ታውክሊያ ሲባሉ :በ512 ዓ ም በአክሱም ከተማ ተወለደ:: እናት እና አባቱም ልጃቸውን ለማስተማር ወደ ዘመዳቸው አባ ጌዴዎን ልከው እንዲማር አደረጉት : ይህም አባት አባ ጌዴዎን ትምህርትን ሊያስተምረው በጀመረ ግዜ መቀበልም ማጥናትም ተሳነው እስከ ብዙ ዘመንም መዝሙረ ዳዊትን ሲማር ኖረ ነገር ግን ከልቡ ማጥናትን እምቢ አለው:መምህሩም አብዝቶ ደበደበው ባሳመመውም ግዜ መታገስ ተሳነው ከአባቶቹ ቤትም ወቶ ዕብነ ሃኪም ወደተቀበረበት ገዳም ሄደ : በውስጡም የወርቅ የብር የልብስ መቀመጫዎች የተመሉ ናቸው: ከአንዲትም ዛፍ አጠገብ ደረሰ ከዚያም አረፈ ትልም ወደ ዛፏ ሲወጣ አየ :ወደ ዛፊቱም እኩሌታ ደርሶ ወደ ምድር ይወድቃል :ሁለተኛም ተመልሶ ወደ ላይ ይወጣል መጀመርያ ወደ ደረሰበት ሲደርስ ይወድቃል:ሲወጣ ሲወድቅ ብዙ ግዜ ያደርጋል : ወደ ሌላ ቦታም አይሄድም
ከዚህም በኋላ በብዙ ጥረት በብዙ ትጋት በብዙ ድካም በዚያ ከዛፏ ላይ ወጣ:ከዚያችም ከዛፏ ላይ ተቀምጦ በላ :ቅዱስ ያሬድም ወደዚያ ዛፍ ላይ ይወጣ ዘንድ እንደሚተጋ ብዙ ግዜም ከላይ ሳይደርስ ከመካከል እንደሚወድቅ ከዚያም በኋላ በጭንቅ ወደ አሰበው እንደደረሰ የፈለገውንም እንዳገኘ የትሉን ትጋት ባየ ግዜ ሰውነቱን ግርፋቱን እንደምን አትታገሺም ህማሙንስ እንደምን አትችይም አላት መታገስንስ አብዝተሽ ኖሮ ቢሆን እግዚአብሄር በገለጠልሽ ነበር ይንንም ብሎ አለቀሰ ወደ መምህሩ ወደ ጌዲዮን ተመለሰ አባት ሆይ ይቅር በለን እንደቀድሞ ንገረኝ አስተምረኝም አለው:መምህሩ ጌዲዮንም እንዳልከው ይሁን አለው 150ውን መዝሙረ ዳዊት:መሃልየ ነብያትን :መሃልየ መሃልይን :የእመቤታችን ድንግል ማርያምን ምስጋና ነገረው:81ዱ መጻህፍትን ትርጓሜ የሌሎች መጽሃፍትን ቁትር እና የመሳሰሉትን መጽሃፍተ ሊቃውንት ሁሉ በአንድ ቀን አጥንቶ ፈጸመ::
ከዚህ በኋላ በብዙ ለቅሶ ወደ እግዚአብሄር በለመነ ግዜ ልቡናው ብሩህ ሆኖለት በአጭር ግዜ የብሉይ እና የሃዲስ መጽሃፍትን ተምሮ ፈጸመና ዲቁና ተሾመ:በዚያም ወራት እንደዛሬ በከፍተኛ ቃል የመዝሙር ማህሌት የለም ነበር በትሁት እንጂ :: እግዚአብሄርም መታሰቢያ ሊያቆምለት በወደደ ግዜ ከኤዶም ገነት 3 አእዋፍን ላከለት እነርሱም በሰው አንደበት ተናግረውት ወደ እየሩሳሌም ሰማያዊት ከእነሱ ጋር አወጡት በዚያም 24ቱ ካህናተ ሰማይ የሚያመሰግኑበትን ማህሌት ተማረ::
ወደ አነዋወሩ ወደ ምድርም በተመለሰ ግዜ በአክሱም ዳር ወደ ከበረች ቤተ ክርስቲያን በ3 ሰዓት ገባ በታላቅም ቃል ሃሌ ሉያ ለአብ:ሃሌ ሉያ ለወልድ: ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ :የፅዮንም ደገኛዋ ሰማይን ፈጠረ ዳግመኛም እንዴት እንደሚሰራት የድንኳንን አሰራር ለሙሴ አሳየው አስተማረው አለ:: ይህቺም ምስጋና አርያም ብሎ ጠራት:የቃሉንም ድምጽ በሰሙ ግዜ ንጉሱም ንግስቲቱም ጳጳሱም ከካህናቱ ሁሉ ጋር የመንግስት ታላላቆች እና ህዝቡ ሁሉ ወደ እርሱ ሮጡ:ሲሰሙትም ዋሉ ከዚህም በኋላ ከአመት እስከ አመት በየክፍለ ዘመኑ በክረምት እና በበጋ:በመጸው እና በጸደይ:በአጽዋማት እና በባእላት :በሰንበታትም እንዲሁም በመላእክት በአል በነብያት እና በሃዋርያት በጻድቃን እና በሰማእታት በደናግልም በአል የሚሆን አድርጎ በሶስቱ ዜማው ሰራ :ይህውም ግዕዝ ዕዝል አራራይ ነው::
የሰው ንግግር የአእዋፍ የእንሥሳትና የአራዊት ጩሀት ከነዚህ ከሶስቱ ዜማ አይወጣም :በአንዲት እለትም ቅዱስ ያሬድ ከንጉስ ገበረመስቀል እግር በታች ቆሞ ሲዘምር ንጉሱም የያሬድን ድምጽ እያዳመጠ ልቡ ተመስጦ የብረት ዘንጉን ወይም መቋምያውን በያሬድ እግር ላይ ተከለው ከእርሱም ደምና ውሃ ፈሰሰ ያሬድም መሃሌቱን እስከሚፈጽም አልተሰማውም ነበር ንጉሱም አይቶ ደነገጠ በትሩንም ከእግሩ ላይ ነቀለ ስለፈሰሰው የደምህ ዋጋ የፈለከውን ለምነኝ ብሎ ለያሬድ ተናገረው ያሬድም ላትከለክለኝ ማልልኝ አለው ንጉስም በማለለት ግዜ ወደ ገዳም ሄጄ እመነኩስ ዘንድ አሰናብተኝ አለው ንጉሱም ሰምቶ ከመኳንንቱ ጋር እጅግ አዘነ ተከዘም እንዳይከለክለውም መሃላውን አሰበ እያዘነም አሰናበተው ከዚ በኋላም ቅዱስ ያሬድ ወደ በተክርስቲያን ገብቶ በታቦተ ጽዮን ፊት ቆሞ ፈጽሞ የከበርሽ እና የተመሰገንሽ ከፍ ከፍ ያልሽ የብርሃን መውጫ የህይወት ማዕረግ የሆንሽ የሚለውን ምስጋና (አንቀጸ ብርሃን) እስከመጨረሻ በተናገረ ግዜ ክንድ ያህል ከምድር ከፍ ከፍ አለ::
ከዚህ በኋላ ወደ ሰሜን ሃገር ሄዶ በጾም በጸሎት ተወስኖ ስጋውን እጅግ እያደከመ ኖሮ ገድሉን በዚያ ፈጸመ እግዚአብሄር ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጠው ከዚ በኋላ ግንቦት 11 ቀን በሰሜን ተራራ አሁን ቅዱስ ያሬድ ገዳም ባለበት ቦታ ተሰወረ :የአባታችን የአምሳለ ሱራፌል የሊቁ ማህሌታይ የቅዱስ ያሬድ ጸሎቱ በረከቱ ረድኤቱ በኛ በህዝበ ክርስቲያኑ ላይ በሃገራችን በኢትዮጵያ ላይ ለዘላለም በእውነት ይደርብን !!!!!አሜን..........................ቸር ያቆየን!

Saturday, May 15, 2010

የበረሃ አባቶች መልዕክት (ከገዳም የመጣ መልዕክት)

1:- ይድረስ ለኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆች:-
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን:
በእግዚአብሄር ቸርነት: በእመቤታችን አማላጅነት: በመላእክት ተራዳይነት: በቅዱሳን ፀሎት: እስከዛሬ በህይወት ሳንጥፋ ላቆየን አምላክ ምስጋና ይግባውና ቀሪ ህይወታችንንም በሰላም በጤና በፍቅር ያቆየን ዘንድ የቸሩ ፈጣርያችን ቸርነት አይለየን እያልኩ ይህችን አጭር እና አብይ መልዕክት አስተላልፋለው እና እግዚአብሄር ቢፈቅድ ሁላችንም በአንድ ላይ ሆነን ለራሳችንም ፍጹም ሰላምን አግኝተን ለሌላው እንድንተርፍ እና ለሃገራችንም እግዚአብሄር ፍጹም ምህረቱን እንዲያወርድልን መንግስተ ሰማያትንም እንዲያወርሰን ሁላችንም ንስሃ እንግባ እላለው!!!!!!!
ንሰሃ ማለት:- ከእግዚአብሄር ጋር መታረቅ ማለት ነው:
ከእግዚአብሄር ጋር መታረቅ ማለት ከሃጥያት ርቆ የእግዚአብሄርን መንገድ ተከትሎ መሄድ ሲሆን: ንስሃ ለመግባት ደግሞ ከልጅነት እስከ እውቀት የሰራነውን ሃጥያት ወደ ካህናት ቀርበን ራሳችንን ገልጸን አንድም ሳናስቀር የበደልነውን ተናዘን ቀኖናችንን መውሰድ ነው:ከዛም የዕለት ኑሮዋችንን እግዚአብሄርን በማስቀደም ማከናወን የሚገባንን ማከናወን ነው::!!!!!!!
2:- ይድረስ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ መንፈሳዊ ማህበሮች እና የጽዋ ማህበሮች:-
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን:
በእግዚአብሄር ቸርነት: በእመቤታችን አማላጅነት: በመላእክት ተራዳይነት: በቅዱሳን ፀሎት:የቤተ ክርስቲያናችን ማህበራት ዛሬ ላይ ደርሳቹ ለምዕመኑ የሃይሞኖትን ፍቅርን እና ጣዕምን እንዲያድርበት አልፎም ቤተ ክርስቲያኖቻችንን እንዲረዱ እንድታደርጉ ለረዳቹ እግዚአብሄር ምስጋና ይሁንና: የበለጠ ደግሞ እግዚአብሄር ፈቅዶ ምዕመኑን ንሰሃ እንዲገባ የበለጠ የእለት የእለት መልዕክታቹ እንዲሆን በእግዚአብሄር ስም እጠይቃለው: ሲጀመርም የመንፈሳዊ ማህበራት የመጀመሪያ አላማ ሰዉን ንሰሃ አስገብቶ በሃይማኖት አጽንቶ ፍጻሜ እንዲያምር ሲሆን ከዛ በመቀጠል ይሆናል እንግዲ ሌላው ሌላው መልእክት መተላለፍ ያለበት እና ሁላችንም ንሰሃ ገብተን እግዚአብሄርን ለመለመን ይርዳን !!!!!!!
3:- ይድረስ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ወንጌል ሰባክያን እና ዘማርያን:-
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን:
በእግዚአብሄር ቸርነት: በእመቤታችን አማላጅነት: በመላእክት ተራዳይነት: በቅዱሳን ፀሎት:የሃዋርያትን:የ72 አርድእትን የተለያዩ የቀደሙ ቅዱሳን አባቶችን ፈለግ ተከትላቹ ለምእመኑ የክርስቶስን ወንጌል እንድትሰብኩ እና ሰዉ በሙሉ ስለ አማናዊው ክርስቶስ እንዲያውቅ እንድታስተምሩ ለረዳችሁ ለእግዚአብሄር ምስጋና ይሁንና: የትኛውም ሰባኪያን ወይም መዘምራን የመጀመርያው አላማው ቤተክርስቲያናችንን ማገልገል ሲሆን ምእመኑንም ወደ ንሰሃ የመምራት ሃላፊነት አለበት:እናም ምእመኑን በተደጋጋሚ ንሰሃ ማስገባት:ስለ ንሰሃ መስበክ የመጀመርያ አርዕስታቹ እንዲሆን በቸሩ እግዚአብሄር ስም እጠይቃለው!!!!!!!
4:- ይድረስ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አባቶች:-
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን:
በእግዚአብሄር ቸርነት: በእመቤታችን አማላጅነት: በመላእክት ተራዳይነት: በቅዱሳን ፀሎት: ስልጣነ ሃዋርያትንም የያዛቹ አይንተ እግዚአብሄር ካህናት ለህዝበ ክርስቲያኑ እረኛ እንድትሆኑ ለራዳቹ ለእግዚአብሄር ምስጋና ይድረስና: ቸሩ ፈጣርያችን እግዚአብሄር እረኛ እንድትሆኑ አድርጎ የረዳችሁን አምላክን ለማገልገል ዘወትር የማትሰንፉ የክርስቶስ አይኖች እኔ ሳይገባኝ የምለምናቹ እውነተኛ እረኛ በጠፋበት በዚህ ሰአት ነገ ዛሬ ሳትሉ እውነተኛ እረኛ እንድትሆኑን ለልጆቻቹ ወደ ንሰሃ መቅረብን የተቻላችሁን እንድታደርጉል ዘወትር በምጠሩት በቸሩ እግዚአብሄር ስም እጠይቃለው !!!!!!!

ማጠቃለያ:- እግዚአብሄር አምላክ ህይወታችንን ሳይወስድ እድሜ ለንሰሃ እየሰጠን መሆኑን አውቀን ከሃጥያት ርቀን አባቶቻችን በተጓዙበት መንገድ ተጉዘን ህይወታችን አምሮ እና ሰምሮ ኋላም ፍጹም መንግስተሰማያትን ለመውረስ ነገ ዛሬ ሳንል ንስሃ እንግባ !!!!!!!
ይህንንም ጽሁፍ ማነው የጻፈው ከየት ነው የመጣው ከሚለው ምንድን ነው የሚለው ላይ አተኩረን እናንብብ:
ወስበሃት ለእግዚአብሄር
ወወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር!!!!!!!
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ ህዝቦቿንም ይጠብቅልን!!!!

Thursday, May 6, 2010

ልደታ ለማርያም :- ክፍል 2

ከዚያም በሁአላ ቅድስት ሃና እና ቅዱስ እያቄም እለቱን ራእይ አይተው ነገር አግንተው አደሩ:ራእዩም እንዴት ነው ቢሉ ኢያቄም 7ቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ አላት:ወፍ የተባለው ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው:ነጭነቱ ንጽሃ ባህሪው ነው:ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ ማለቱ:የኢያቄምን ባህርይ ባህርይ እንዳደረገው እወቅ ሲል ነው:7ቱ ሰማያት የተባሉ የጌታችን ልዩ ልዩ ባህሪው:ምልአቱ:ስፍሃቱ:ርቀቱ:ልእልናው:ዕበዩ መንግስቱ ናቸው:ሃናም እኔም አየሁ አለችው:ምን አየሽ ቢላት:ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማህጸኔ ስትተኛ አየሁ አለችው::ርግብ የተባለች እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት:ነጭነቱአ ንጽህናዋ:ቅድስናዋ ድንግልናዋ ነው:ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማህጸኔ ስትተኛ አየሁ ማለቱአ ብስራተ ገብርኤልን በጆሮዋ ሰምታ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችንን መፀነሱአ ነው:ይህንኑም ራእይ ያዩት ሃምሌ 30 ዕለት ነው::
እነሱም እንዲ ያለ ራዕይ ካየን:ነገር ካገኘን ብለው ዕለቱን በሩካቤ ሥጋ አልተገናኙም:ፈቃደ እግዚአብሄር ቢሆን ብለው አዳምንና ሄዋንን ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሉአት ብሎ ያበሰረ አምላክ ለኛስ ይልክልን የለምን? ብለው ዕለቱን አልጋ ምንጣፍ ለይተው እስከ 7 ቀን ድረስ ለየብቻቸው ሰነበቱ:ነሃሴ በባተ በሰባተኛው ቀን ከሰው የበለጠች ከመላእክት የከበረች ዓለሙ ሁሉ ተሰብስቦ ቢመዘን አንድ የራሱአን ፀጉር የማያህል ደግ ፍጥረት ትወልዳላቹህና ዛሬ በሩካቤ ስጋ ተገናኙ ብሎአቹሃል ጌታ ብሎ መልአኩ ለሃና ነገራት በፈቃደ እግዚአብሄር በብስራተ መልአክ እመቤታችን እግዝእትነ ማርያም እሁድ እለት ተፀነሰች(በኦሪት ስርአት እሁድ ዕለት ባል እና ሚስት መገናኘት ልማድ ነበርና):እመቤታችን የተፀነሰች ዕለት አይሁድ ቀንተው ተነሱባቸው ቅናቱ እንዴት ነው ቢሉ:ሳሚናስ የሚባል የጦሊቅ ልጅ ከኤዶቅ ካጎቱ ቤት ሄዶ ሞተ እነርሱም እንቀብራለን ብለው ባልጋ ይዘው ሲሄዱ ከመንገድ አሳረፉት:የሃናም የአጎቱአ ልጅ ነበርና ለማልቀስ ብትደርስ ዘመዶቹአ ሁሉ ተሰብስበው ሲላቀሱ ቆዩአት:እርሱአም አብራ እየዞረች ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ብድግ ብሎ ተነስቶ ስብሃት ለኪ ማርያም እሙ ለፀሃየ ጽድቅ ለአብ ሙሽራው ለወልድ ወላዲቱ ለመንፈስቅዱስ ጽርሃ ቤቱ ተፈስሂ ደስ ይበልሽ ብሎ ሰገደላት:አይሁድ ከዛ ነበሩና ምነው ሳሚናስ ምን አየህ? ምን ትላለህ? ቢሉት ከዚች ከሃና ማህፀን የምትወለደው ህፃን ሰማይ ምድርን:እመቅ አየርን የፈጠረ አምላክን ትወልዳለች እያሉ መላእክት ሁሉ ሲያመሰግኑአት ሰማሁአቸው እኔንም ያነሳችኝ የፈወሰችኝ ያዳነችኝ እርሱአ ናት አላቸው በል ተወው ሰማንህ ብለው ቅናት ጀመሩ::
""እመቤታችን እግዝትእነ ማርያም በተፀነሰች በ9 ወር ከአምስት ቀን የግንቦት መባቻ ዕለት ግንቦት 1 ተወለደች::""
እመቤታችን እግዝትእነ ማርያም የተወለደችበት እለት በአባት እናቱአ ቤት ፍስሃ ደስታ ተደረገበት ቤቱንም ብርሃን መላው በስምንተኛውም ቀን ""ማርያም"" ብለው አወጡላት::ስለምን ማርያም ብለው አወጡላት ቢሉ:እነሆ በዚ አለም ከሚመገቡት ሁሉ ምግብ ለአፍ የሚጥም ለልብ የሚመጥን "ማር" ነው:በገነትም በህይወት የተዘጋጁ ጻድቃን ቅዱሳን "ያም" የሚባል ምግብ አላቸው ::ከዚ ሁሉ የበለጥሽ የከበርሽ ነሽ ሲሉ ስለዚህ "ማርያም" ብለው አወጡላት::የእመቤታችን ማርያም ስም ተነቦ ሳይተረጎም ይቀር ዘንድ አይገባምና:-""ማ"" ማለት ማህደረ መለኮት: ""ር"" ማለት ርግብየ ይቤላ: ""ያ"" ማለት ያንቀዓዱ ኃቤኪ ኩሉ ፍጥረት:""ም"" ማለት ምስሃል ወምስጋድ ወምስትሥራየ ኃጥያት ማለት ነው::አንድም "ማርያም" ማለት ልዩ ከጣዖት:ክብርት እምፍጥረታት:ንጽህት እምሃጥያት:መልክ ከደም ግባት የተሰጣት ማለት ነው:ዳግመኛም "ማርያም" ማለት ተፈስሂ ቤተ ይሁዳ ወተሃሠዪ ቤተ እስራኤል ማለት ነው::
አንድም "ማርያም" ማለት መርህ ለመንግስተ ሰማያት ማለት ነው:ይህስ እንዴት ነው ቢሉ:እነሆ ዛሬ በዚህ አለም ለዕውር መሪ በትር እንዲሰጡት ሁሉ እርሱአም በፍቅሩአ:በጣዕመ ፍቅሩአ የሰውን ሁሉ ኃጥያት:ክፋት ፍቃ ከልጁአ ከወዳጁአ አስታርቃ ከገሃነመ እሳት አውጥታ መንግስተ ሰማያት የምታስገባ ስለሆነች ስለዚህ መርህ ለመንግስተ ሰማያት አሉአት::አንድም ማርያም ማለት ሰረገላ ፀሃይ ማለት ነው:አንድም ማርያም ማለት ተላኪተ እግዚአብሄር ወሰብእ ማለት ነው:አንድም ማርያም ማለት ውብህት(ስጥውት) ማለት ነው::
በዚህ በግንቦት አንድ ቀን እመቤታችን አለምን ልታስምር ከቅድስት ሃና እና ከቅዱስ እያቄም በብዙ ልመና ተገኘች::
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ፍቅሩአ ጣዕሙአ በረከቱአ ረድኤቱአ አማላጅነቱአ በእውነት በኛ አማላጅነቱአን በምናምን ልጆቹአ ላይ ይደርብን::
""አለም ያለ ወላዲተ አምላክ አማላጅነት አይድንም""...................ቸር ያቆየን!!!

ልደታ ለማርያም :- ክፍል 1

ጴጥርቃ እና ቴክታ የሚባሉ ሰዎች በኢየሩሳሌም በአንድነት ተጋብተው ይኖሩ ነበር:እነዚህም በእግዚአብሄር የሚያምኑ የተወደዱ ጻድቃን ደግ ሰዎች ነበሩ:እነዚህም ሰዎች በእግዚአብሄርም በሰውም ዘንድ የበቁ ባለጸጎች ነበሩ:ነገር ግን የሚወርሳቸው ልጅ አልነበራቸውምና መካን ነበሩ:አንድ ቀን ጴጥርቃም ቴክታን እህቴ ሆይ ይህን ሁሉ የሰበሰብነውን ገንዘባችንን ምን እናደርገዋለን ልጅ የለን የሚወርሰን:አንቺም መካን ነሽ እኔም ካንቺ በቀር ሌላ ሴት አላውቅም አላት:እርሱአም ወንድሜ ሆይ አምላከ እስራኤል ለኔ ልጅ ቢነሳኝ አንተም እንደኔው ሆነህ ትቀራለህን? ከሌላ ደርሰህ ውለድ እንጂ ብላ ብታሰናብተው እንደዚ ያለ ነገር እንኩአንስ ላደርገው በልቦናዬ እንዳላስበው አምላከ እስራኤል ያውቅብኛል አላት:እሱአም አምላከ እስራኤል የሚያደርገውን የሚያውቅ የለም:ትላንትና ማታ በህልሜ ነጭ ጥጃ ከማህጸኔ ስትወጣ ያችም ነጭ ጥጃ ሌላ ነጭ ጥጃ ስትወልድ እንዲሁ እስከ 7ት ትውልድ ሲዋለድ ሰባተኛይቱ ጨረቃን ስትወልድ ጨረቃዋም ፀሃይን ስትወልድ አየሁ አለችው::
እርሱም በጠዋት ከህልም ፈቺ ዘንድ ሂዶ የነገረችውን ሁሉ ነገረው:ያም ህልም ፈቺ እግዚአብሄር በምህረቱ አይቱአቹአል በሳህሉ መግቡአችሁአል 7 አንስት ጥጆች መውለዳቹ 7 ሴቶች ልጆች እና የልጅ ልጆች ትወልዳላቹ ከቤታቹ ሰባተኛይቱ ጨረቃ መውለዱአ ከሰው የበለጠች ከመላእክትም የከበረች ደግ ፍጥረት ትወልዳላቹ የፀሃይ ነገር ግን አልታወቀኝም አለው:እርሱም የነገረውን ሁሉ ሄዶ ነገራት እርሱአም እንጃ አምላከ እስራኤል የሚያደርገውን ማን ያውቃል ብላ ዝም አለች:ከዛም ፀንሳ በ9 ወሩአ ሴት ልጅ ወለደች:ስሙአንም ሄሜን ብለው አወጡላት:ሄሜንም አድጋ ለአካለ መጠን ስደርስ አጋብተዋት ሴት ልጅ ወለደች በስምንተኛ ቀኑአም ደርዲ ብለው ስም አወጡላት:ደርዲም አድጋ እንዲሁ ሴት ወለደች እና ቶና አለቻት:ቶናም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሲካር አለቻት;ሲካርም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሴትና አለቻት:ሴትናም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሄርሜላ አለቻት:ሄርሜላም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ንጽህት ቅድስት ክብርት የምትሆን እመቤታችንን የምትወልደውን ሃናን ወለደች::
ከጴጥርቃና ከቴክታ የተወለዱ 67 ወንዶች ልጆች አሉ የእመቤታችን የድንግል ማርያምን ትውልድ ለመቁጠር ትንቢት አልተነገረላቸውም ሱባኤ አልተቆተረላቸውምና አልተፃፈም:ይህቺም ሃና በስራት በቅጣት አደገች:ለአእምሮ ስትበቃ አካለ መጠን ስደርስ ከቤተ መንግስት ወገን ከነቅዱስ ዳዊት ወገን ከሆነው(መጽሃፍ ቅዱስ ይገልጸዋል) ከቅዱስ እያቄም ጋር አጋቡአት::እነዚህ ቅዱሳን እያቄም እና ሃና በአንድነት ተጋብተው ሲኖሩ ልጅ አጡ:ከእለታት አንድ ቀን ወደ ቤተ እግዚአብሄር ሂደው ሲፀልዩ ሲያዝኑ ዋሉ:ሃዘናቸው እንዴትስ ነው ቢሉ:እያቄም:-"አቤቱ ጌታዬ ያባቶቼ የእስራኤል አምላክ እኔ ባርያህ እለምንሃለው አትጣለኝ:አትናቀኝ:ፀሎተን ስማኝ ፈቃዴን ፈጽምልኝ:ለአይኔ ማረፊያ ለልቤ ተስፋ የሚሆን የተባረከ ወንድ ልጅ ስጠኝ" ብሎ ሲለምን ዋለ:ሃናም በበኩሉአ "አቤቱ ጌታዬ የአባቶቼ የእስራኤል አምላክ እኔ ባርያህ እለምንሃለው:ስማኝ ለአይኔ ማረፊያ ለልቤ ተስፋ የምትሆነኝ የተባረከች ሴት ልጅ የማህፀኔን ፍሬ ስጠኝ" ብላ ስትለምን ዋለች: እንዲ ብለው ስይዝኑ ሲጸልዩ ውለው ርግብ ከልጆቹአ ጋር ስትጫወት አይታ አቤቱ ጌታዬ ለዚች ግእዛን ለሌላት እንስሳ ልጅ የሰጠህ አምላክ ምነው ለኔ ልጅ ነሳኅኝ ብላ ምርር ብላ አለቀሰች:እንዲ ብለው ሲያዝኑ ሲፀልዩ ውለው ከዘካርያስ ከሊቀ ካህናቱ ሄደው አቤቱ ጌታችን ሆይ ወንድ ልጅ ብንወልድ ተምሮ ቤተ እግዚአብሄርን አገልግሎ እንዲኖር እንሰጣለን:ሴት ልጅም ብንወልድ ማይ ቀድታ መሶብ ወርቅ ሰፍታ መጋረጃ ፈትላ ካህናትን አገልግላ እንድትኖር እንሰጣለን ብለው ስለት ገቡ::
ዘካርያስም እግዚአብሄር ጸሎታችሁን ይስማላቹ ስእለታችሁን ይቀበልላቹ ጻህቀ ልቦናችሁን ይፈጽምላቹ ብሎ አሳረገላቸው:የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም እናቶች እና አባቶች በረከት ይደርብን!!!!!.........ይቆየን

Wednesday, May 5, 2010

አቡነ ዘርዓ ብሩክ

የጻድቁ አባታችን የዘርዓ ብሩክ አባት እና እናት የተባረኩ ከቅዱሳን ወገን የሚሆኑ ነበሩ የአባታቸው ስምም ቅዱስ ደመ ክርስቶስ ሲባል እናታቸው ደግሞ ቅድስት ማርያም ሞገሳ ትባላለች ጻድቁ አባታችን ገና በናታቸው ማህጸን እያሉ ነበር ብዙ ተአምራት የሚያደርጉት እግዚአብሄር መርጡአቸዋልና በሁአላም ከክርስቶስ ልደት በሁአላ በስምንተኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ ላይ በነሃሴ 27 ጻድቁ አባታችን ተወለዱ በ40ኛ ቀናቸውም ተጠምቀው በካህናት አፍ "ጸጋ ክርስቶስ" ተባሉ ከዛም ቤተሰቦቻቸው በጥሩ እድገት አሳደጉአቸው 7 አመትም በሞላቸው ግዜ በልጅነቴ የዚን አለም ክፋቱን እንዳላይ ብለው ቢጸልዩ አይናቸው ታውሩአል:ቤተሰቦቻቸውም የዚን አለም ትምህርት ሊያስተምሩአቸው አስተማሪ ጋር ቢወስዱአቸው ታመው ተመልሰዋል:የእግዚአብሄር ፈቃድ አይደለምና ነገር ግን የሚያስፈልጋቸውን እውቀት ፈጣሪ አምላክ ራሱ ገልጾላቸዋል:: ክህነትን እስከ ጵጵስና እራሱ መድሃኒአለም ክርስቶስ ሰቶአቸዋል:12 አመትም በሞላቸው ግዜ አይናቸው በርቶላቸው ታላላቅ ተጋድሎን ማድረግ ጀመሩ : የሃጥያት ማሰርያን ያስሩና ይፈቱ ዘንድ ጵጵስናን በሾማቸው ግዜ እግዚአብሄር ያወጣላቸው ሁለተኛ ስም "ዘርዓ ብሩክ" ይባል ነበር 3ኛውም ስማቸው ደግሞ "ጸጋ እየሱስ"ይባላል::
ጻድቁ አባታችን በዚ አለም በህይወተ ስጋ ሳሉ አቡቀለምሲስ እንደሚባል እንደ ዮሃንስ ወልደነጎድጉአድ እግዚአብሄር እሱ ወዳለበት ወደ ሰማይ አውጥቶ በገነት መካከል ያኖራቸው ነበር:: እግዚአብሄር አምላክ ለወዳጁ ለብጹዕ አባታችን ዘርዓ ብሩክ በጎ ነገር እንዳደረገለትና ያለ ድምጽ የሰማይ ደጆችን አልፎ የእሳት ባህርን ተሻግሮ ፈራሽ በስባሽ ሲሆን እንደ ህያዋን መላእክት በፍጥነት ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ከአድማስ እስከ አድማስ ይደርስ ዘንድ 12 ክንፍን ሰጣቸው:መላእክትም ለሌሎች ቅዱሳን ያልተሰጠ ይህንን ስልጣን አይተው ለምድራዊ ሰው ይህ ነገር እንዴት ይቻላል እያሉ አደነቁ: ከዛም በሁአላ ጻድቁ አባታችን ከፈጣሪ ዘንድ የመላእክትን አስኬማ,የሾህ አክሊል አምሳያ የሆነውን መንፈሳዊ ቆብን,ሰማያዊ ቅናትን እና የደረት ልብስን(ስጋ ማርያም) ተቀብሎ በጾም እና በጸሎት በልመና እና በስግደት እግዚአብሄርን ሲያገለግል ኖረ ከዛም በላይ ወንጌልን እጅግ ብዙ በማስተማር ደከመ ከኢትዮጵያም አልፎ ግብጽ ድረስ ገባ የእስክንድርያውን ሊቀ ፓፓስ አባ ዮሃነስን አገኘውና እርስ በርስ ሰላምታን ተለዋውጠው እጅ ተነሳሱ ከዛም ተመልሶ ወደ ሃገሩ መጣ ከዛም ኢትዮጵያ ውስጥ እየተመላለሰ ወንጌልን አስተማረ እጅግ ስጋን በሚያስጨንቅ ትጋትም የኢትዮጵያን ህዝብ ማርልኝ እያለ እያለቀሰ ይጸልይ ነበር: አንድ ቀን አባታችን በንጉስ ጭፍሮች ተይዘው ሲሄዱ ዳዊታቸውን ለግዮን ወንዝ አደራ ሰተዋት ከ5 አመት በሁአላ ሲመለሱ ግዮን ሆይ ዳዊቴን ግሺ መልሺሊን ቢሉአት አንድም የውሃ ጠብታ ሳይኖርባት ዳዊታቸውን ብትመልስላቸው ለደቀ መዝሙራቸው ዘሩፋኤል አሳዩትና ግዮንንም "ግሽ አባይ" ብለውታል እስካሁንም በዚሁ ስም የሚጠራው ከዚ በመነሳት ነው::
ከዚህም ሌላ ጻድቁ አባታችን በዚሁ ወንዝ አካባቢ ለ 30 አመት ሲጸልዩ ፈጣሪ አምላክ ጸሎታቸውን ሰምቶ እጅግ ልዩ የሆነ ቃል ኪዳን ሰቶአቸዋል:በስተመጨረሻም የሚያርፉበት እለት በደረሰ ሰአት መልአከ ሞት መቶ እስኪደነግጥ እና ወደ ሁአላው እስኪያፈገፍግ ድረስ ነው ነው እግዚአብሄር ጸጋውንና ክብሩን ያበዛላቸው: በስተመጨረሻም ጥር በገባ በ13 ቀን በ482 አመታቸው ስጋቸው ከነፍሳቸው ተለይታ ገነትን ወርሰዋል::ምንጭ ገድለ አቡነ ዘርዓ ብሩክ የጻድቁ አባታችን ገድለ ዜና እንኩአን በዚች በምታህል ጽሁፍ አይደለም የገድላቸውም መጽሃፍም አልበቃውም እንደው እግዚአብሄር አምላክ ከበረከታቸው እንዲያሳትፈን አስቤ ይችን ጥቂት የገድላቸውን ዜና ከገድላቸው መጽሃፍ ላይ አስቀመጥኩ:ለእግዚአብሄር ምስጋና ይሁን እኛንም በኚህ ጻድቅ ጸሎት ይማረን በረከታቸውንም ያድለን አሜን... ........ቸር ያቆየን !!!!!

Sunday, May 2, 2010

አባ መቃርስ

አባ መቃርስ በግብጽ ደቡብ መኑፍ ከሚባል አውራጃ ሳሱይር ከሚባል መንደር ከሚኖሩ ሰዎች ወገን ነው:ወላጆቹም ደጎች እውነተኞች ነበሩ አባቱም አብርሃም እናቱም ሳራ ይባላሉ:እናቱም እንደ ኤልሳቤጥ እና ሳራ በእግዚአብሄር ትዛዝ ጸንታ የምትኖር ናት አባቱም በፈሪአ እግዚአብሄር ሆኖ ንጽህናውን እና ቅድስናውን ጠብቆ ሁል ግዜ ቤተ ክርስቲያንን በማግልገል ፀንቶ ይኖራል:እግዚአብሄርም በላያቸው በረከቱን አሳድሮ በስራቸው ሁሉ ከፍ ከፍ አደረጋቸው:ለድሆችም የሚመጸውቱ ለሰው ሁሉ የሚራሩ ናቸው:በፆም በፀሎት ተወስነው እንዲ ባለ ገድል ሲኖሩ ግን ልጅ አልነበራቸውም ለአብርሃምም በለሊት ራእይ ከእግዚአብሄር ዘንድ በልጅ አምሳል ተገለጠለት በአለም ሁሉ የሚታወቅ ብዙ መንፈሳውያን ልጆችን የሚወልድ ልጅን ይሰጠው ዘንድ እግዚአብሄር እንደወደደ ነገረው:ከዚም በሁአላ ይህ የከበረ ልጅ መቃርስን እግዚአብሄር ሰጠው ትርጉአመውም ብፁእ ማለት ነው በላዩም የእግዚአብሄር ፀጋ አደረበት:ለወላጆቹም ይታዘዝ እና ያገለግል ነበር ባደገ ግዜ ያጋቡትም ዘንድ አሰቡ እርሱ ግን ያን አይሻም ነበር ፈቃዳቸውን ይፈፅም ዘንድ ግድ ብለው አጋቡት:ወደ ሙሽራይቱም በገባ ግዜ ራሱን እንደታመመ ሰው አደረገ እንዲሁም ሆኖ ብዙ ቀን ኖረ:ከዚአም በሁአላ አባቱን ተወኝ ወደ ገዳም ልሂድ ከበሽታዬ ትንሽ ጤናን ባገኝ አለው:እግዚአብሄር ወደ ሚወደው ስራ ይመራው ዘንድ ሁል ግዜ በፆም እና በፀሎት ሆኖ ይለምነው ነበር:ከዚህም በሁአላ ወደ አስቀጥስ በረሃ ሄደ ከበረሃው በገባ ግዜ ራዕይን አየ:ስድስት ክንፍ ያለው ኪሩብ እጅና እግሩን ይዞ ወደ ተራራው ላይ እንደሚያወጣው እና የአስቀጥንስ በረሃ ምስራቁአን ምዕራቡአን የዚአችን በረሃ አራት መአዘኑአን አሳይቶ እነሆ ይችን በረሃ መላዋን ላንተ እና ለልጆችህ እርስት አድርጎ እግዚአብሄር ሰቶሃል አለው:ከበረሃውም በተመለሰ ግዜ ያቺ ብላተና ሚስቱ ታማ አገኛት ጥቂት ቆይታ በድንግልናዋ እንዳለች አረፈች:የክብር ባለቤት እግዚአብሄርን አመሰገነ:ከጥቂት ከኖች በሁአላ እናት አባቱም አረፉ:የተውለትንም ገንዘብ በሙሉ ለድሆች እና ለጦም አዳሪዎች ሰጠ:የሳሱይር ሰዎች ግን እውነተኛነቱን እና ቅድስናውን አይተው ቅስና አሾሙት:ከከተማውም ውጪ ቤት ሰሩለት ቅዱስ ስጋውን እና ክቡር ደሙን ይቀበሉ ዘንድ ወደ እሱ ይሄዱ ነበር:
በዚአች አገርም አንዲት ድንግል ብላቴና ነበረች ከአንድ ጎልማሳ ጋርም አመንዝራ ፀነሰች ጎልማሳውም አባትሽ ድንግልናሽን ማን አጠፋው ብሎ ሲጠይቅሽ መቃርስ የሚባለው ባህታዊ ቄስ እሱ ስለ ደፈረኝ ነው በይው ብሎ መከራት ፅንሱአም በታወቀ ግዜ አባቱአ ይህን አሳፋሪ ስራ ባንቺ ላይ የሰራብሽ ማነው ብሎ ጠየቃት:እሱአም በአንዲት ቀን መቃርስ ወደሚባለው ቄስ ሄጄ ሳለው በሃይል ይዞኝ ከኔ ጋር ተኛ እናም ከሱ ፀነስኩ ብላ መለሰችለት:ወላጆቹአም በሰሙ ግዜ እጅግ ተቆጡ ከብዙ ሰዎችም ጋራ ወደ ቅዱስ መቃርስ ሄደው ይዘው ከበአቱ አወጡት እሱ ግን ምን እንደሆነ አላወቀም ነበር:ለመሞት እስኪቃረብም አጽንተው ደበደቡት እሱም ሃጥያቴ ምንድን ናትና ነው እናንተ ያለ ርህራሄ ትደበድቡኛላቹና እያለ ይጠይቃቸው ነበር:ከዚህ በሁአላ በፍም የጠቆሩ ገሎችን ባንገቱ ላይ በገመድ አንጠልጥለው ወዲያ እና ወዲ እየጎተቱ የልጃችንን ድንግልና ያጠፋ ይህ ነው እያሉ እንደ እብድ በላዩ ይጮሁ ጀመር:የዚያን ግዜ መላዕክት እንደሰው ተገልጠው የሚያሰቃዩትን ሰዎች ይህ ተጋዳይ ምን አደረገ አሉአቸው እነሱም በልጃቸው ላይ የሃፍረትን ስራ እንደሰራ አድርገው መልሰው ነገሩአቸው እነዚያ መላዕክትም ይህ ነገር ሃሰት ነው እኛ ይህን ሰው ከታናሽነቱ ጀምሮ እንከዚ ቀን እናውቀዋለን:እሱ የተመረጠ ፃድቅ ሰው ነውና አሉአቸው:የታሰረበትንም ፈተው ከላዩ ላይ ገሎቹን ጣሉ እነዚያ ክፉዎች ግን ዋስ እስከሚሰጠን ድረስ አንለቀውም አሉ እጅ ስራውን የሚሸጥለት አንድ ሰው መጣ ለልጅቱአም በየግዜው ምግቡአን ሊሰጣት ዋስ ሆነው ከዚያ በሁአላ አሰናብተው ወደ በአቱ ተመልሶ ገባ ከዚያች ቀን ጀምሮ ራሱን በራሱ መቃርስ ሆይ"እነሆ እንግዲ ባለ ሚስት እና ባለ ልጅ ሆነሃል ለሊት እና ቀን መስራት ይገባሃል" እያለ ያቺ ሃሰተኛ ልጅ የምትወልድበት ግዜ እስኪደርስ ድረስ እንቅቦችን ቅርጫቶችን እየሰራ ለዚያ ወዳጅ ለሆነውና ለሚያገለግለው ወንድም ይሰጠውና ያም ሰው እየሸጠ ለዚያች ሃሰተኛ ልጅ እየሰጠ ኖረ::
የምትወልድበት ቀን ሲደርስ እጅግ አስጨነቃት በታላቅ ሲቃይ ውስጥ አራት ቀኖች ያህል ኖረች ለሞትም ተቃረበች እንቱአም ካንቺ የሆነው ምንድን ነው የተሰራ ስራ አለና ንገሪኝ አለቻት እሱአም በ እግዚአብሄር አገልጋይ ላይ ዋሽቻለውና ያመነዘርኩት ከእከሌ ጎልማሳ ጋር ሲሆን በ እውነት ሞት ይገባኛል አለቻት:አባት እና እናቱአም በሰሙ ግዜ ደንግጠው እጅግ አዘኑ የሃገር ሰዎችም ሁሉ ተሰበሰቡ በርሱ ላይ የሰሩትን በደል ይቅር ይላቸው ዘንድ ወደ ቅዱስ መቃርስ ሄደው ለመኑት ያን ግዜ በበረሃ ያየውን ያንን ራዕይ አስታውሶ ይቅር አላቸው ቀድሶም ቅዱስ ስጋውንንና ክቡር ደሙን አቀበላቸው:ክንፉ ስድስት የሆነ ኪሩብ ደግሞ ተገለጠለት ትርጉአመውም የልብ ሚዛን ወደተባለ ወደ አስቀጥስ በረሃ እጁን ይዞ መርቶ አደረሰው:ቅዱስ መቃርስም ያንን ኪሩብ ጌታዬ ሆይ በውስጡ የምኖርበትን ቦታ ወስንልኝ አለው ያ ኪሩብም አልወስንልህም የ እግዚአብሄርንም ትዛዝ አትተላለፍ እነሆ ይህ በረሃ ሁለመናው ላነተ ተሰቱአል እና ወደ ፈለክበት ሄደህ ተቀመጥ ብሎ መለሰለት:ቅዱስ መቃርስም የቅዱሳን ሮማውያን የመክሲሞስና የደማቴዎስ ቦታ ወደ ሆነው ከውስጠኛው በረሃ ገብቶ ኖረ:እነሱም በመጥኡ ግዜ ከርሱ አቅራቢያ ኖረዋልና ከረፍታቸው በሁአላ ግን ሄዶ በዚያ ቦታ እንዲኖር የ እግዚአብሄር መልአክ አዘዘው:ይህውም ዛሬ የሱ ገዳም የሆነው መላእኩ ይህ ገዳም በመክሲሞስ እና በደማቴዎስ በስማቸው ይጠራልሥላለው እስከዚች ቀን ደብረ ብርስም ተብሎ ይጠራል ትርጉአመውም የሮም ገዳም ማለት ነው:የከበረ አባ መቃርስም ታናሽ በአት ሰራ በውስጡአም ሆኖ ያለ ማቁአረጥ በጾም በፀሎት በስግደትም በመትጋት ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ ሰይጣናትም ተገልጠው የሚመጡበትን እና በቀንም በለሊትም በግልጽ የሚዋጉት ሆኑ:በጾም እና በጸሎት ሲጋደል ሰይጣናት እየተዋጉት እርፍትን ስላላገኘ በልቡም እንዲ አሰበ በአለም ውስጥ ሳለው የቅዱስ አባ እንጦንዮስን ዜና ሰምቻለው የምንኩስናን ስራት ያስተምረኝ እና ይመራን ዘንድ ተነስቼ ወደሱ ልሂድ የረከሱ ሰይጣናት የመከሩትን ምክራቸውን እገለብጥ ዘንደ እሱ እውቀትን እና ማስተዋልን ይሰጠኛልና አለ ያን ግዜም ተነስቶ ጸሎት አድርጎ ወደ አረጋዊ አባ እንጦንዮስ ዘንድ እስከሚደርስ ወደ ምስራቅ አቅጣጫ ተጉአዘ አባ እንጦንዮስም ከሩቅ ባየው ግዜ እነሆ ተንኮል ሽንገላ የሌለበት ክርስቲያን አለው በታላቅ ደስታም ተቀብሎ ሳመው:አባት ለልጁ እንደሚገልጥ ሃሳቡን ሁሉ ገለጠለት ይህ አረጋዊ አባ እንጦንዮስም የመቃርስን ራሱን ስሞ ልጄ ሆይ በዮናኒ ቁአንቁአ እንደ ስምህ ትርጉአሜ አንተ ብጹእ ትባላለህ ስራህንና ወደኔ መምጥትህን ፈጣሪ እግዚአብሄር ገልጦልኛል እና ስለዚህ መመጥትህን የምጠባበቅ ህንኩ አለው::
ከዚም በሁአላ ለአባ መቃርስ የከበረች የምንኩስናን ስራት አስተማረው መሰራት በሚገባ በብዙ ነገርም አጸናው ሰይጣናት የሚዋጉት መሆናቸውን እነሱም በስውር በፈቲው ጦር እንዲሁም ጥፋት በሆኑ ስራዎች ሁሉ ይዋጉሃል:አንተ ፍፁም ልትሆን አንተም እስከሞት ደርሰህ ታገስ አሁንም እግዚአብሄር ወደ ወሰነልህ ቦታ ሄደህ ስራህን እየሰራህ በውስጡም ታገስ ብሎ ገለጠለት:ከአባ እንጦንዮስ ዘንድ የምኩስናን ስራት እየተማረ ጥቂት ቀኖች ከኖረ በሁአላ ከተባረከ ኤጲስ ቆጶስ ከአባ ሰራብዮን ጋራ በተማራቸው ህያዋን በሚያደርጉ ትምህርቶች እና ስራቶች ፈጽሞ ደስ እያለው ወደ በአቱ ተመለሰ:
አባ መቃርስም በአባቴ በአባ እንጦንዮስም ዘንድ በነበርኩባቸው ቀኖች ሲተኛ ከቶ አላየውትም አለ:አባ መቃርስም በምንኩስና ስራት ተጠምዶ እየተጋደለ ብዙ ግዜ ኖረ ያ ኪሩብ መላእክም በግልጽ ይጎበኘው ነበር:በአንዲት ቀንም እንዲ የሚለውን ቃል ከሰማይ ሰማ ቃሌን እና ትእዛዘን ሰምተህ ወደዚህ መተህ በዚ ቦታ ውስጥ ስለኖርክ እነሆ ቁጥር የሌላቸውን የብዙ ብዙ ወገኖችን ከነገዶች ከሃገሮች በቁአንቁአ ከተለያዩ ህዝቦች እሰበስባለው እነሱም በዚ ቦታ ያገለግሉኛል የከበረ ስሜንም ያመሰግናሉ በበጎ ስራቸው እና ትሩፋታቸው ደስ ያሰኙኛል አንተም ተቀበላቸው እውነተኛ የድነት መንገድም ምራቸው ይሄንንም ቃል በሰማ ግዜ ተበረታታ ልቡም ፀና በለሊቲም በጸሎት ግዜ ቆሞ ሳለ የክብር ባለቤት ጌታችን ጆሮውን ከፍቶለት ሰይጣናት ሲማከሩ ሰማቸው እንዲህም አሉ ይህን ሰው በዚ በረሃ እንዲኖር ብንተወው የብዙ ብዙ ወገኖችን ይመራቸዋል እንሱም በዚ በረሃ ውስጥ ነዋሪዎች ሆነው የሰማይዋን ሃገር ያደርጉታል እንሱ ለዘላለም ጸንቶ በሚኖር ህይወት ይተማመናሉና እኛንም በሚቀጣ ጸሎታቸው ቀጥተው አሰቃይተው ያሳድዱናልና ከዚ ቦታ ልናሳድደው እስኪ እንችል እንደሆነ ኑ ዛሬ ብሱ ላይ እንሰብሰብ ሲሉ ሰማቸው አባ መቃርስም ይህንን በሰማ ግዜ ልቡ ጸና በሰይጣናት ላይም ተበረታታ የሰይጣናት ምክራቸውን እስከሚሰማ ጆሮውን የከፈተለት እግዚአብሄርን አመሰገን:ደካማነታቸውንም አወቀ ::
ከዚ በሁአላ ይዋጉት ዘንድ ሰይጣናት በርሱ ላይ ተሰበሰቡ በደጁ እሳትን እያነደዱ ከሳቱ እያነሱ ወደ በአቱ ይጨምሩ ጀመር ያቺ እሳት ግን በጸሎቱ የሚጠፋ ሆነች ከዚ በሁአላ እንሣዊ በሆነ ስራ በፍትወት(ዝሙት)ጦር ተውጉት በዚም ታገሰ:ትካዘን አለማዊ ክብር መውደድን ትቢትን መመካትን ታካችነትን ስድብን ሃይማኖት ማጣትን ከእግዚአብሄር ዘንድ ተስፋ መኩረጥን በልቡ አሳደሩበት ከዚ ሁሉ በሚበዛ ተዋጉት የከበረ አባት አባ እንጦንዮስ እንደነገረው በኝህም አጥፊዎች በሆኑ ስራዎች ሰይጣናት እየተዋጉት ረጅም ግዜ ከኖረ በሁአላ ዳግመኛ ወደ አባት እንጦንዮስ ተነስቶ ሄደ ይህም አባት ገና ከሩቅ ሳለ ለደቀ መዛሙርቱ በልቡ ሽንገላ በእውነት የሌለበት ክርስቲያን ነው ልጆቼ ይህን የከበረ ሰው ታዩታላቹን እሱ ለብዙ ወገኖች የቀና የጽድቅ በትር እና ረጅም አላማ ይሆን ዘንድ አለውና:ከአሸናፊ እግዚአብሄር አፍ የተገኘ ጣፋጭ ፍሬም ይሆናልና አለ:ወደ ቅዱስ አባ እንጦንዮስም በቀረበ ግዜ በምድር ላይ ሰገደለት በፍጥነትም ቀና አድርጎ ሳመው ፊቱ እንደበሽተኛ ፊት ተለውጦ አይቶታልና ይህውም ሰይጣናት አብዝተው ስለተዋጉት ነው:ከዚያም ጸሎት አድርገው በአንድነት ተቀመጡ አባት እንጦንዮስ ደስታ በተመላ ቃል ልጄ መቃርስ በደና አለህን? አለው ቅዱስ መቃርስም እነሆ ከኔ የሆነውን ሁሉ እግዚአብሄር ቀድሞ ገልጦልሃል ብሎ መለሰለት:እሱም ያን ግዜ አስተማረው አጽናናው እንዲህም ብሎ መከረው:መንፈሳዊ ጥበብን ለሚሹ ለብዙ ወገኖች መምህራን እንድትሆን ይህቺውም ምንኩስና ናት ከጠላታችን በላያችን የሚመጣብንን መከራ ሁሉ ልንታገስ ለኛ የሚገባ ነው ልጄ መቃርስ ሆይ ውሃ ለመቅዳት ስትሄድ እግዚአብሄር የነገረህን ያንን ቃል አስብ አለው:ቅዱስ መቃርስም ሰምቶ እጅግ አደነቀ የተሰወሩ ስራዎቹ በከበረ አባት ለ እንጦንዮስ የተገለጡለት እንደሆኑ አወቀ በርሱ ዘንድም እየተማረና በረከትን እየተቀበለ ብዙ ቀኖች ኖረ ከዚያም የከበረች አስኬማን ያለብሰው ዘንድ ፈለገ አባ እንጦዮስም በላዩ ጸለየ እርሱአን አስኬማይቱን አለበሰው ስለዚ የከበረ እንጦንዮስ አባት ተባለ::
ዳግመኛም ወደዚህ ወደኔ መመጣትን ቸል አትበል እኔ ከጥቂት ቀኖች በሁላ ወደ እግዚአብሄር ሄዳለውና አለው አባ መቃርስም ይህንን ነገር በሰማ ግዜ ተነስቶ ሰገደለት መንፈሳዊ በረከቱን ይቀበል ዘንድ ከርሱም ዘንድ እንዲኖር ለመነው እሱም ተቀመጥ አለና ተቀመጠ:ዳግመኛም አባ እንጦንዮስ ከጥቂት ቀኖች በሁአላ ሰይጣናት በኔ ላይ እንዳደረጉት በግልጥ ከተዋጉህ በሁአላ ከዚ ከክፉ ሃሳብ ውጊአ እግዚአብሄር ያሳርፍሃል እና በርትተህ ታገስ:እስከ እድሜህ ፍጻሜ ካነተ ጋር ሆኖ እንዲረዳህ እግዚአብሄር ያደረገውን ጠባቂሂን መልአክ እንዳታሳዝነው ተጠበቅ አለው:ከዚ በሁአላ አባ እንጦንዮስ ለአባ መቃርስ በትሩን ሰጠው በመንፈሳዊ ሰላምታ ተሰናብቶት አረፈ:ሲጋውንም ማንም በማያቀው ስውር ቦታ ቀበረው:የከበረ አባ መቃርስም ወደ በአቱ ተመልሶ በአስቀጥስ ገዳም ተቀመጠ ዜናውም በአራቱ መአዘን ተሰማ እግዚአብሄርም በጆቹ አስደናቂዎች ተአምራትን አደረገ::
ከዚህ በሁአላ የከበረ አባ መቃርስ ተመልሶ ከርሱ አስቀድሞ በዚያ አስቄጥስ በርሃ ውስጥ ሰው እንዳለ ያይ ዘንድ ወደ በረሃ ውስጥ ዘልቆ ገባ:ራቁታቸውን የሆኑ ሁለት ሰዎች አይቶ ፈራ የሰይጣን ሚትሃት መስሎታልና 'እልቦት' 'ቦሪቦን' ብሎ በህቡ የ እግዚአብሄር ስም ጸለየ ይህም አቡነ ዘበሰማያት ማለት ነው:እንሱም በስሙ ጠርተው መቃርስ ሆይ አትፍራ አሉት እርሱም በበረሃ የሚኖሩ ቅዱሳን እንደሆኑ አውቆ ወደነሱ ቀርቦ እጅ ነሳቸው እነሱም በአለም ስላሉ ሰዎች ስለ ስራቸው ጠየቁት እርሱም በቸርነቱ እግዚአብሄር በሁሉም ላይ አለ ብሎ መለሰላቸው:እርሱም ደግሞ የክረምት ቅዝቃዘ ይቀዘቅዛቸው እንደሆነ የበጋውን ትኩሳት ያያልባቸው እንደሆነ ጠየቃቸው እነሱም በዚ በረሃ እግዚአብሄር 40 አመት ጠብቆናል የክረምት ቅዝቃዜ ሳይቀዘቅዘን የበጋ ትኩሳት ሳያቃጥለን ኖረናል ብለው መለሱለት:ደግሞ እነደናንተ መሆነ እንዴት እችላለው አላቸው እነሱም ወደ በአትህ ተመልሰህ ስለሃጥያትህ አልቅስ አንተም እንደኛ ትሆናለህ አሉት:ከነሱም በረከትን ተቀብሎ ወደ በአቱ ተመለሰ::
በርሱ ዘንድ መነኮሳት በበዙ ግዜ ጉድጉአድ ቆፍረው መታጠቢያ ሰሩለት ሊታጠብ በወረደ ግዜ ሊገሉት ሰይጣናት ጉድጉአዱን በላዩ ላይ አፈረሱት መነኮሳትም መተው ከጉድጉአዱ አወጡት:እግዚአብሄርም ከዚ አለም መከራ ያሳርፈው በወደደ ግዜ ሁልግዜ የሚጎበኘውን ኪሩብን ወደ እርሱ ላከ እርሱም እኔ ወዳንተ መጥቼ ወስድሃለው እና ተዘጋጅ አለው ከዚያ በሁአላ አባ እንጦንንንና የቅዱሳንን አንድነት መሃበርን ሰማያውያን የሆኑ የመላእክት ሰራዊትን በ እግዚአብሄር እጅ ነፍሱን እስከሰጠ ድረስ ያይ ነበር:መላ የእድሜው ዘመንም 97 ሆነ መጋቢት 27 ቀንም ከዚ ከአላፊው አለም ወደማያልፈው አለም ነፍሱ ሄደች: የቅዱስ መቃርስ ነፍስ ወደ ሰማይ ስታርግ እንዳየ በዚ ነገር ደቀ መዝሙሩ አባ በብኑዳ ምስክር ሆነ:ሰይጣናትን እንደሰማቸው እየተከተሉ መቃርስ ሆይ አሸነፍከን አሸነፍከን እያሉ ሲጮሁ እስካሁን ገና ነኝ አላቸው ወደ ገነት ሲገባ መቃሪ ሆይ አሸነፍከን ብለው በታላቅ ድምጽ ጮሁ የክብር ባለቤት ፈታሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ይመስገን ስሙም ይባረክ ከእጃቹ ያዳነኝ አላቸው:ብሎ መስክሮአል:የስጋውም ፍልሰትም እንደዚ ሆነ እሱ በህይወት ሳለ ስጋውን እንዳይሰውሩ ልጆቹን አዙአቸው ነበር የሃገሩ የሳሱይርም ሰዎች መተው ለደቀ መዝሙሩ ለዮሃንስ ገንዘብ ሰጡ ይንንም ስለገንዘብ ፍቅር ይመክረው እና ይገስጸው የነበረ ገንዘብ ከመውደድ ተጠበቅ የሚለው ነው:እርሱም መርቶ የቅዱስ አባ መቃርስን ስጋ አሳያቸው ወደ ሃገራቸው ሳሱይር ወሰዱ እስከ አረብ መንግስት 160 ዘመን በዚያ ኖረ ደቀ መዝሙሩ ዮሃነስ ግን ገንዘብ ስለመውደዱ ዝልጉስ ሆነ::
ከዚያም በሁአል ልጆቹ መነኮሳት ወደ ሃገሩ ወደ ሳሱይር ሄዱ የከበረ አባት የአባ መቃርስን ስጋ ሊወስዱ ፈለጉ:የሃገሩ ሰዎችም ከመኮንኑ ጋር ተነስተው ከለከሉአቸው በዚያችም ለሊት የከበረ አባ መቃርስ ለመኮንኑ ተገልጦ ተወኝ ከሊጆቸ ጋር ልሂድ አለው መኮንኑም መነኮሳቱን ጠርቶ የአባታቸውን ስጋ ተሸክመው ይወስዱ ዘንድ ፈቀደላቸው:በዚአን ግዜም ተሸክመው አክብረው ወሰዱት በብዙ ምስጋና በመዘመርም እግዚአብሄርን እያመሰገኑ ነሃሴ 19 ቀን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖሩት ከሱም ታላላቅ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ::
ለእግዚአብሄር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አባ መቃርስ እና በአባ እንጦንዮስ ፀሎት እና አማላጅነት የምትገኝ በረከት ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች እንዲሁም ከሃገራችን ከኢትዮጵያ ጋር ለዘላለም ይኑር አሜን!!!!!!...................ቸር ያቆየን.

Saturday, May 1, 2010

ተአምረ ጊዮርጊስ

ተአምረ ጊዮርስ 12ኛ ተአምር:- ፀሎቱና በረከቱ ልመናው ለሁላችን በእውነት ለዘላለሙ ይደረግልንና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረገው ተአምር ይህ ነው:: በፍጹም ልቡ ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚወድ በግብጽ ሃገር የሚኖር አንድ ሰው ነበረ ከፍቅሩም ብዛት የተነሳ እጅግ ያማረ ቤተ ክርስቲያን አሳነፀ:የእግዚአብሄርንም የህጉን ታቦት ለማስገባት በፈለገ ግዜ አንድ ከሃዲ ንጉስ መጣና ከሚስቱ ጋር ከቤተ ክርስቲያኑ ገብቶ መኖሪያውን በዚያ አደረገ:ሰውየውም በችኮላ ሄዶ ይህንን ነገር ለሊቀ ጳጳሱ ነገረው ሊቀ ጳጳሱም ተነስቶ ወደ ንጉሱ ሄደና ለምን የማይገባ ስራ ከቤተ ክርስቲያን ገብተህ ስለምን ትቀመጣለህ ቤተ ክርስቲያኒቱ የታነፀችው በሃያሉ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ነውና አለው::ንጉሱም ይህንን ንግግር ሰምቶ እጅግ ተቆጣና ያስረው ይገርፈውም ዘንድ ወደደ ሊቀ ጳጳሱም እጅግ አዘነና አይኖቹን ወደሰማይ አቅንቶ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሃያሉ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲ ሲል አዳኘው:"ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ እኔ ሰማዕት ነኝ አትበል:በዚህ በአላዊ ንጉስ ላይ ሃይልህን የማትገልጽ ከሆነ ከማህበረ ሰማዕት ሁሉ ጋራ በእግዚአብሄር ፊት አትቁም":ሊቀ ጳጳሱም ይህንና የመሳሰለውንም ሁሉ እየተናገረ ሳለ ሃያሉ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ በግልጽ እያዩት በነጭ ፈረስ ተቀምጦ በሰማይ ላይ እንደ እሳት እያንበለበለ በድንገት ከተፍ ብሎ ወደ ከሃዲው ንጉስ ገባና በጦር ወግቶ ከዙፋኑ ገለበጠው ከቤተ ክርስቶያኑም ሩቅ በሆነ ቦታ ወስዶ በምድር ላይ ዘረረውና በዚያን ግዜ ክፉ ሞት ሞተ:ሚስቱም እንዲሁ:የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረቱን ሁሉ በተነው ከቶ ምንም የተረፈ አልነበረም::በዚያም የነበሩ ሰዎች ሁሉ ታላቅ ፍርሃት ወደቀባችው ፈጽመውም አደነቁ ሊቀ ጳጳሱም ከተደረገው ተአምራት የተነሳ ደነገጠ ፈጽሞም አደነቀ:ከዚህም በሁአላ ሃያሉ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ጳጳሱን ከገዘትከኝ ግዝት ፍታኝ አለውና ፈታው::ነዚያን ግዜም በስሙ ከታነፀው ቤተ ክርስቲያን በፍጹም ደስታ በምስጋናና በዝማሬ በሃያሉ ሰማዕት በቅዱስ ጊዮርጊስ እጅ ሃይሉን የገለፀውን እግዚአብሄርን እያመሰገኑ ታቦተ ህጉን አስገቡ::ፀሎቱና በረከቱ አማላጅነቱ ለሁላችን በዕውነት ይደረግልን ለዘላለሙ አሜን!!!!!...........ቸር ያቆየን.