Friday, August 6, 2010

ውዳሴ ማርያም አንድምታ ዘቀዳም :- ክፍል 1

ውዳሴሃ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ዘይትነበብ በዕለተ ቀዳሚት ሰንበት
በክብር ትቀድማለችና:: አንድም በዕለተ ሰንበት አይሁድ የሚል አብነት ይገኛል አይሁድ በብሉይ የሚያከብሯት ሲል ነው :: በዚህም ቀን እመቤታችን ትመጣለች :: የብርሃን ድባብ ይዘረጋል የብርሃን ምንጣፍ ይነጠፋል :: ከዚያ ላይ ሁና ሰላም ለከ ኦፍቁርየ ኤፍሬም ትለዋለች :: እርሱም ታጥቆ እጅ ነስቶ ይቆማል:: ወድሰኒ ትለዋለች ክርክር አልቋልና :: ባርክኒ ይላታል :: በረከተ ወልድየ ወአቡሁ ወመንፈስቅዱስ ይህድር በላዕሌከ ትለዋለች :: ተባርኮ ምስጋናዋን ይጀምራል ::ውዳሴ ዘቀዳሚት ዉዳሴ በቀዳሚት ዉዳሴሃ ለእግዝትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ዘይትነበብ በዕለተ ቀዳሚት ሰንበት ይላል ቃለ ጸሐፊ ነው :: እርሱ ግን ንጽህት ወብርህት ብሎ ይጀምራል ::
" ንጽህት ወብርህት"
ንጽህት ነሽ ብርህት ነሽ ::
" ወቅድስት በኩሉ::"
በአፍኣ በውስጥ ንጽህት ነሽ : እርሷ የምትለወጥ ሁና አይደለም : እርሱ እየቀደመ እየበቃ ማየቱን መናገር ነው ::
" እንተ ሐቀፈቶ ለእግዚእ በእራሃ :"
ጌታን በማሃል እጅሽ የያዝሺው : ህጻናትን አናት ይወርድላቸዋልና ብለው በማሃል እጃቸው እንዲይዟቸው :: አንድም በክንድሽ የያዝሽው ::
" ወኩሉ ፍጥረት ይትፌሥሑ ምስሌሃ "
ፍጥረት ሁሉ ካንቺ ጋር እንዳንቺ ደስ ይላቸዋል :: እንዘ ይጸርሁ ወይበሉ
" ሰአሊ ለነ ቅድስት "
እያሉ አንድም ተፈስሒ ኦ ምልዕተ ጸጋ ::ምልዕተ ክብር ሆይ ( ተፈሥሒ) ደስ ይበልሽ እያሉ ::
" ተፈሥሒ እስመ ረከብኪ ሞገር ተፈሥሒ እግዚአብሔር ምስሌኪ :"
እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነስቶ ካንቺ ጋር አንድ ባህርይ ቢሆን ባለሟልነትን አግኝተሻልና ( ተፈሥሒ) ደስ ይበልሽ ::
" ናስተበፅዕ ዕበየኪ ኦ ግርምት ድንግል "
ግርምት ድንግል ክብርሺን ገናንነትሽን ዕፁብ ዕፁብ እያልን እናመሰግናለን :: ግርምትነትቷ በአይሁድ በመናፍቃን በአጋንንት ዘንድ ነው ::
" ወንፌኑ ለኪ ፍሥሐ ምስለ ገብርኤል መልአክ :"
ከመልአኩ ጋራ እንደ መልአኩ ምስጋና እናቀርባለን :: ምስጋናውን ፍስሐ አለው : ተፈሥሒ ተፈሥሒ እያለ ነውና ::
" እስመ እምፍሬ ከርሥኪ ኮነ መድሃኒተ ዘመድነ :"
ከማህፀንሽ ፍሬ የባህሪያችን ድህነት ተገኝቷልና አንድም የማህፀንሽ ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስ የባህሪያችን ድህነት ሆኗልና ::
" ወአቅረበነ ሃበ እግዚአብሔር አቡሁ :"
ከአባቱ ጋራ አስታረቀን " ሰአሊ ለነ ቅድስት "
ካባቱ ጋራ ካስታረቀን ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን ::
" ከመ ከብካብ ዘአልቦ ጥልቀት :"
እንደ ሰርግ ቤት አደፍ ጉድፍ የሌለብሽ ሆነሽ ቢያገኝሽ :
" መንፈስቅዱስ ሃደረ ላዕሌኪ "
መንፈስቅዱስ አድሮብሻልና :
" ወሃይለ ልዑል ጸለለኪ:"
ሃይለ ልዑል ወልድም ሥጋሽን ለብሷልና አንድም መንፈስቅዱስ ከሦስቱ ግብራት ከልክሎሻልና ሃይለ ልዑል ወልድም ከሦስቱ ግብራት ከልሎሻልና
" ኦ ማርያም አማን ወለድኪ ቃለ ወልድ አብ ዘይነብር ለዓለም :"
ለዘላለም ጸንቶ የሚኖር አካላዊ ቃልን ወለድሽልን :
"መጽአ ወአድሃነነ እምሃጢያት:"
ሰው ሆኖ ከሃጢያት አዳነን አንድም ከሃጥያታችን ፍዳ ያዳነን " ሰአሊ ለነ ቅድስት "
ሰው ሆኖ ከሃጥያታችን ፍዳ ካዳነን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን ::
" አንቲ ውእቱ ዘመድ ዘእምሥርወ ዳዊት:"
ከዳዊት ሥርው የተገኘሽ ባህርይ አንቺ ነሽ :ሥር ወደላይም ወደታችም ያድጋል ወደላይ ቢሉ ዕሴይ ወደታች ቢሉ ኢያቄም መገናኛው ዳዊት ::
" ወለድኪ ለነ በሥጋ መድሃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ :"
መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋ ወልደሽዋልና :
" ዋህድ ቃል ዘእምአብ ዘእምቅድመ ዓለም ህልው :"
ቅድመ ዓለም የነበረ ከአብ ባህርይ ዘእምባህርይ አካል ዘእምአካል የተወለደ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አካላዊ ቃል :
" ሃብአ ርእሶ :"
ባህርዩን በስጋ ቢሰውር:
" ወነስአ እምኔኪ አርኣያ ገብር :"
ከአንቺ አርአያ ገብርን ቢነሳ መድሃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ወልደሽልናልና : አንድም ቅድመ ዓለም ህቡዕ የሚሆን አካላዊ ቃል ህብዓ ርእሶ ባህርዩን በስጋ ሠወረ :ካንቺም ሃየሰ ወረሰ ከብረ ተለዓለ ነገሠ መባልን ገንዘብ አደረገ : " ሰአሊ ለነ ቅድስት "
ሃየሰ ወረሰ ከብረ ተለዓለ ነገሰ ከሚባል ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን ::
" ኮንኪ ዳግሚተ ሰማይ ዲበ ምድር :"
ከምድር በላይ ያለሽ ሁለተኛ ሰማይ አንቺ ነሽ : አንድም ከምድር በላይ ያለች የጠፈር ባልንጀራ ሆንሽ :
" ኦወላዲተ አምላክ ዘእንበለ ርኩስ:ሠረቀ ለነ እምኔኪ ፀሐየ ጽድቅ:ዘእንበለ ዘርዕ ወኢሙስና : ሰአሊ ለነ ቅድስት :"
አደፍ ጉድፍ ሳይኖርብሽ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ፀሐየ ጽድቅ ጌታ ካንቺ ተወልዷልና ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው እንደተናገሩ : ዘር ምክንያት ሳይሆንሽ መለወጥ ሳያገኝሽ ወልደሽዋልና : ዘር ምክንያት ሳይሆንሽ ከወለድሽው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን ::
"አንቲ ውእቱ ደብተራ እንተ ተሰመይኪ ቅድስተ ቅዱሳን:ወውስቴታ ጽላተ ኪዳን:መሶበ ወርቅ እንተ መና ህቡዕ:ዘውእቱ ወልደ እግዚአብሔር መጽአ ወሃደረ ሃበ ማርያም ድንግል "
ከተለዩ የተለየሽ ከከበሩ የከበርሽ ደብተራ አንቺ ነሽ :ሕግ የተጻፈበት ኪዳን ያለብሽ: መና ያለበት መሶበ ወርቅ ያለብሽ:ይህውም ሰው ሆኖ በማህጸንሽ ያደረው ወልደ እግዚአብሔር ነው : ደብተራ የእመቤታችን ምሳሌ ቅድስት የነፍሷ ምሳሌ ቅዱሳን የ4ቱ ባህርያት ምሳሌ ታቦት የመንፈስቅዱስ ጽላት የልቦናዋ ቃሉ በመንፈስቅዱስ የተገለጸላት ምሥጢር :: አንድም ቅዱሳን የሥጋዋና የነፍሷን : ቅድስት የልቦናዋ : ታቦት የማህጸኗ ጽላት : የትስብእት ቃሉ የመለኮት ምስሌ :
" ተሰብአ እምኔሃ ቃለ አብ : ወወለደቶ ውስተ ዓለም ለንጉሠ ስብሐት : መጽአ ወአድሃነነ :ትትፌሣህ ገነት እመ በግዕ ነባቢ :"
አካላዊ ቃል ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆነ :የክብር ባለቤት እርሱን በዚህ ዓለም ወለደችው : ሰው ሆኖ ያዳነን : የነባቢ በግዕ እናቱ ደስ ይላታል ኢነባብያን አባግዕ አሉና ከዚያ ሲለይ በግዕ ነባቢ አለ : አንድም 7ቱን አጽራሐ መስቀል የተናገረውን ሲል በግዕ ነባቢ አለ :
" ወልደ አብ ዘይነብር ለዓለም : መጽአ ወአድሃነነ እምሃጥያት : ሰአሊ ለነ ቅድስት :"
ለዘላለሙ ጸንቶ የሚኖር አካላዊ ቃል ሰው ሆኖ ከሃጥያት ያዳነን አንድም ከሃጥያታችን ፍዳ ያዳነን :ሰው ሆኖ ከሃጥያታችን ፍዳ ካዳነን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን:: ይቆየን የቅዳሜን ክፍል 2 በሚቀጥለው ሳምንት እንመለስበታለን.............ቸር ያቆየን !!!!!

No comments:

Post a Comment