Saturday, August 7, 2010

ውዳሴ ማርያም አንድምታ በዕለተ ሰንበት እሁድ ክፍል 1

ውዳሴሃ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ዘይትነበብ በዕለተ ሰንበተ ክርስቲያን::
ሰንበት አይሁድ አለችና ከዚያች ሲለይ ሰንበተ ክርስቲያን አለ :ያውስ በከንቱ ነውን ወበዛቲ ዕለት እሙነ ተፈጸመ እንዲል ሁለቱን ቀን የሚያከብር የሆነ እንደሆነ ዓርብ ከሰዓት ይወጣል እሁድ በሰዓት ይወርዳል::አንዱን ቀን የሚያከብር እንደሆነ ቅዳሜ ከሰዓት ይወጣል እሁድ ከሰዓት ይወርዳል: እንዲህ እያለ ሲኖር ጌታ የሚመጣው በዕለተ እሁድ ነውና እንደወጣ ይቀራል: በዚህም ቀን እመቤታችን ከወትሮው ጊዜዋ ቀደም ብላ መጥታ ለምንት ኢወደስከኒ በዛቲ ዕለት አለችው ከወትሮው ጊዜዋ ቀደም ብላ ከመጣች ስለምን ለምንት ኢወደስከኒ አለችው ቢሉ የህሊናውን አውቃ: እሱም በገድል ተቀጥቅጦ ነዋሪ ስለሆነ ጥቂት ወይን ጠጥቶ ዕረፍት ሽቶ ነበርና: ጳውሎስ ጢሞትዮስን ህዳጠ ወይነ ቶስሕ በእንተ ሕማመ ከብድከ ወበእንተ ደዌከ ዘዘልፍ እንዳለው:ዛቲ ዕለት ዓባይ ወክብርት አላት: ዛቲ ዕለት ተዓቢ እምኩሎን ውዳሴያት አለችው ከዚህ በኋላ ባርክኒ ይላታል በረከተ ወልድየ ወአቡየ ወመንፈስቅዱስ ይህድር በላዕሌከ ትለዋለች: ተባርኮ ምስጋናዋን ይጀምራል በዚህም ቀን በቤተ መቅደስ ባሉ ንዋያት በመሶብ ወርቅ በማዕጠንተ ወርቅ በበትረ አሮን እየመሰለ ሲያመሰግናት አድሯል ::
"ተሰመይኪ ፍቅርተ ኦ ቡርክት እምአንስት:አንቲ ውእቱ ዳግሚት ቀመር እንተ ትሰመይ ቅድስተ ቅዱሳን: ወውስቴታ ጽላተ ኪዳን:"
ንዕድ ክብርት ሆይ ከሴቶች ተለይተሽ የሥላሴ ባለሟል ተባልሽ : ከተለዩ የተለየሽ ከከበሩ የከበርሽ ቅዱሳን ኪሩቤል የተሳሉብሽ ቅዱሳን ካህናት የሚያመሰግኑሽ ሁለተኛ ክፍል አንቺ ነሽ: ህግ የተጻፈባት ጽላት ያለብሽ ሕጉን ኪዳን ይለዋል ብትጠብቁት ይጠብቃችኋል ብሎ ተከይዶበታልና::
"10ቱ ቃላት እለ ተጽሕፋ በአጻብዒሁ ለእግዚአብሔር: ቀዲሙ ዜነወነ በየውጣ እንተ ይእቲ ቀዳሜ ስሙ ለመድሃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ::"
ኪዳንም ያልሁት በአፃብዐ እግዚአብሄር የተጻፉ ዐሥሩ ቃላት ናቸው በግብር አምላካዊ ስለተገኙ በአፃብዐ እግዚአብሄር አለ: ከስመ ሥጋዌም የሚቀድም ስሙን በየውጣ ነገረን: ከስመ ስጋዌ የሚቀድም ስሙን : ኢታምልክ ባዕደ አምላክ ዘእንበሌየ ብሎ በዮድ ፊደል ነገረን አለ: ዮድ ለአሌ ዐሥረኛ እንደሆነች ኢታምልም ለኢትፍቱ ዐሥረና ናትና: አንድም ከስመ ሥጋዌው የሚበልጥ አሙን በየውጣ ነገረን አለ:ቀዳሜ ፍጥረት ብሄሞት ቀዳሚሆሙ ለአህዛብ አማሌቅ እንዲል: የውጣ በሃገራቸው ዕዝል ቅጽል የላትም አንድ ጭራ ናት: ዐሠርቱም በሃገራችን ዕዝል ቅጽል የላትም አንድ ጭራ ናትና: አንድም ዋሕድ ቃለ እግዚአብሔር በአፃብዐ መንፈስቅዱስ በማህጸኑዋ እንዲቀረጽ ዐሠርቱ ቃላትን በጽላቱ ጽፎ በማኖሩ ነገረን:ታሪክ:- እስራኤል ከግብጽ ከወጡ በኋላ ሙሴ አሮንና ሖርን ከተማ ጠባቂ አድርጎ ኢያሱን አስከትሎ ደብረሲና ሄዶ ስድስት ቀ ቃል ለቃል ይነጋገረዋል: ሠላሳ ዐራት ቀን በልቦናው የሳለበትን እየነገረ ያጽፈዋል: ከዚህም በኋላ ሙሴ ቢዘገይባቸው እስራኤል ከአሮን ዘንድ ሄደው አሮን አሮን ግበር ለነ አማልክተ እለ የሐውር ቅድሜነ ወእለ ይፀብዑ ፀረነ እስመ ዝኩሰ ሙሴ ዘአውጻነ እምድረ ግብጽ ኢነአምር ከመ ምንተ ኮነ :አመሌ አመሌ ሲል ደብረ ሲና ያየው እሳትም በልቶት እንደሆነ ወደ ኤርትራ ተመልሶ ሄዶ አስጥማው ቀርቶም እንደሆነ ሙሴ የሆነውን አናቅምና ጣዖት ስራልን አሉት: እሱም እምቢ ብላቸው እስራኤል ቁጡአን ናቸው በደንጊያ ወግረው ይገድሉኛል: ይሁንም ብላቸው ፈጣሪዬ ይጣላኛል ብሎ እስራኤል ሃብት ወዳጆች ናቸው ከዛሬ ነገ ሲሉ ወንድሜ ይመጣልኛል ከነገር እድናለው ብሎ ሴቶችንም ወንዶችንም ከግብጽ ያወጣችሁትን ገንዘባችሁን አምጡ አላቸው: ሰይጣን አነሳስቷቸዋል እና እንዋል እንደር ሳይሉ ዕለቱን አመጡለት ጉድጓዽ አስምሶ እሳት አስነድዶ ከዚያ ላይ አስጣለው: ከዚህ በኋላ አንድ ቀንዱ የወርቅ አንድ ቀንዱ የብር ጅራቱ የሃር የሆነ ምስል መቶ ቆመ:ይህስ ምትሃት ይመስላል ብሎ ተድበልብሎ ወጣ እሱ ቅርጽ አውጥቶ አሰርቶታል::
ከዚህ በኋላ በፍና ተሳልቆ ጌሰም በዓለ እግዚእ ብሎ አዋጅ ነገረ : ከዚህ በኋላ መስዋዕቱን በልተው ሲዘፍኑ ሲያጨበጭቡ: ሙሴ ሙሴ አበሱኒ እስራኤል ሕዝብከ:አለው ጸብ ተጀመረ ህዝብየ ይላቸው የነበረ ሕዝብከ አለው አባት ልጁን ሲጣላ ያ ልጅሽ እንዲህ አደረገ እንዲል:ሰንኪያስ ወርደህ ሥራ ቅፃ አለው: ከዚህ በኋላ ዓሥሩን ቃላት በጽላት ጽፎ ሰጠው ያን ተቀብሎ እያሱን አስከትሎ ሲሄድ እስራኤል ጉሽ ጠጅ ጠጥተው ይዘፍናሉ ያጨበጭባሉ: የአርበኛ የሰልፈኛ ድምጽ አይደል አለው;ቢደርስ ከዚያ ጣዖቱን አቁመው ተረፈ መስዋዕቱን በልተው ሲሰግዱ አየ ቢደነግጥ ከእጁ ወድቆ ጽላቱ ተሰበረ: ዛሬ ከቄስ እጅ ጥና ወድቆ እንዲሰበር አንድም በጽላቱ ጣዖቱን መታው ጣዖቱም ጽላቱም ተሰበረ ከዚህ በኋላ ወርቁን አስፈጭቶ ከፈሳሽ ባህር አስበጥብጦ ጠጡ አላቸው: ፍቅረ ጣዖት ያደረበት ከከንፈሩ ከግንባሩ እንደ ለምጽ ተቀረጸበት: ይህን ምልክት አድርጎ ሌዋውያንን ከበር አቁሞ በሏቸው አትማሯቸው: አባት ልጁን ልጅ አባቱን ወንድም ወንድሙን አይማረው ብሎ 3000ሺህ ሰዎች አስፈጅቷል: አንፈስክዎ ለእግዚአብሔር እስኪላቸው ድረስ: ከዚህ በኋላ ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክት ቀር ከመ ቀዳምያት አለው: የቀደመውን አስመስለህ አምጣ አለው ይዞ ሄዶ ቃሉ በግብር አምላካዊ ተገኝቷልና ይህውም ምሳሌ ነው: የቀደመው ጽላት የአዳም ሁለት መሆኑ የስጋውና የነፍሱ በግብር አምላካዊ መገኘቱ አዳም እንበለ ዘርዕ ለመገኘቱ ምሳሌ: የኋለኛው ጽላት የእመቤታችን ሁለት መሆኑ የስጋዋና የነፍሷ: ቀር ከመ ቀዳምያት አለው: እመቤታችን በዘር ለመገኘቷ ምሳሌ:ቃሉ የጌታ ምሳሌ በግብር አምላካዊ መገኘቱ: ጌታ እንበለ ዘርዕ ለመገኘቱ ምሳሌ: የቀደመው ጽላት የዕንቁ ነው የኋለኛው ጽላት ዕብነ በረድ ነው::
"ዘተሰብአ እምኔኪ ዘእንበለ ውላጤ:ወኮነ አራቄ ለሐዲስ ኪዳን:በውሂዘ ደሙ ቅዱስ አንጽሆሙ ለመሃይምናን ወለሕዝብ ንጹሃን:"
ካንቺ ሳይለወጥ ሰው የሆነ ለወንጌል ሊቀ ካህናት ለመንግስተ ሰማያት አስታራቂ ሆነ: ሐዲስ ኪዳን ወንጌል ብሉይ ኪዳን ኦሪት:ሐዲስ ኪዳን መንግስተ ሰማያት ብሉይ ኪዳን ምድረ ርስት: በከበረ ደሙ ፈሳሽነት በዓለመ ስጋ በዓለመ ነፍስ ያሉትን አዳናቸው: አንድም በዕለተ ዓርብ በቀኖት የፈሰሰውን ደሙን መላዕክት በአውራ ጣታቸው ተቀብለው እረጭተውታል:ይህንስ ያህል አይደፍሩም ብሎ በጽዋዓ ተቀብለውታል: ዛሬ ቤተክርስቲያን የሚሰራበት ደሙ የፈሰሰበት ቦታ ነው: ታሪክ:- ጳልቃን ጣልቃን የሚባሉ አዕዋፍ አሉ ልጆቻቸውን ይወዳሉተንከባክበው አቅፈው ያኖሩዋቸዋል ልጆቹ ተጫወትን ብለው ፊታቸውን ይጸፉታል ይሰማቸዋል ራሳቸውን ቆርጠው ይገድሏቸዋል ከዚህ በኋላ በሦስተኛው ቀን ከናታቸው ካባታቸው ጎን ቢሉ ደም አውጥተው ቀብተው ያስነሷቸዋል: ጳልቃን ጣልቃን የተባሉ ሥላሴ ናቸው ልጆቻቸውን ተንከባክበው እንዲያኖሩዋቸው በገነት አዳምንና ሄዋንናክብረው አኖሯቸው ተጫወትን ብለው ፊታቸውን እንዲጸፉ አምላክነትን ሲፈልጉ ተገኝተዋል: ራሳቸውንም ቆርጦ እንደመግደል በሞተ ስጋ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ርደተ ገሃነም ፈርደውባቸዋል በሦስተኛውም ቀንከናታቸው ካባታቸው ጎን ቢሉ ደም አውትተው ቀብተው እንዲያስነሷቸው: አንተ አቡነ ወአንተ እምነ የሚባል ጌታ ከጎኑ ደሙን አፍስሶ ለማዳኑ ምሳሌ " ሰአሊ ለነ ቅድስት"
በከበረ ደሙ ፈሳሽነት በዓለመ ስጋ በዓለመ ነፍስ ያሉትን ካዳነ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኚልን
"ወበእንተዝ ናዓብየኪ ኩልነ ኦ እግዝእትነ ወላዲተ አምላክ: ንጽህት ኩሉ ግዜ:ንስህል ወናንቀዓዱ ሃቤኪ :ከመ ንርከብ ሣህለ በሃበ መፍቀረ ሰብእ:"
መጽሃፍ ላለፈውም ለሚመጣውም አጸፋ ይሰጣል: አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ስለዚህ ነገር ሁላችን እናከብርሻለን እናገንሻለን:ንጽህት ኩሎ ጊዜ ንስህል ኩሎ ጊዜ ብሎ ይገጥማል: ሁልግዜ ንጽህት የምትሆኚ:ሁልጊዜ አይነ ልቦናችንን ወዳንቺ እንሰቅላለን: ሰውን ከሚወድ ሰው ከሚወደው ከርሱ ይቅርታን እናገኝ ዘንድ::
"ታቦት ዘወርቅ ልቡጥ እምኩለሄ ዘግብር እምዕፅ ዘኢይነቅዝ: ይትሜሰል ለ ዘእግዚአብሔር ቃል:"
ሸምሸር ሸጢን ከሚባል ከማይነቅዝ እንጨት የተቀረጸ በአፍአ በውስጥ በወርቅ የተለበጠ ታቦት: አካላዊ ቃልን ይመስልልናል አንድም መመሳሰል የጋራ ነው ብሎአካላዊ ቃል ታቦትን ይመስልልናል: ታቦት የእመቤታችን ምሳሌ: (ዕፅ ዘኢይነቅዝ) የአብርሐም:ዘኢይነቅዝ አለው በአምልኮተ ጣዖት አይለወጥምና: አንድም ታቦት የጌታ ምሳሌ ዕፅ ዘኢይነቅዝ የእመቤታችን ዘኢይነቅዝ አከ በሃጥያት አትለወጥምና አንድም ታቦት የጌታ ምሳሌ:ዕፅ ዘኢይነቅዝ የአብ: አሁን ዘግቡር ሲል ያውካል::
"ዘኮነ ሰብአ ዘእንበለ ፍልጠት ወኢውላጤ: መለኮት ንጹህ ዘአልቦ ሙስና:ዘዕሩይ ምስለ አብ: ወቦቱ አብስራ ለንጽህት::"
መለወጥ ሳያገኘው መለየት ሳያገኘው ሰው የሆነ:ንጹህ ከተፈልጦ ከተድህሮ አንድም ንጹህ ካለመመለክ ንጹህ የሚሆን መለወጥ የሌለበት በአብ ዕሪና ያለብባለመለወጡ አለመለወጡአን: ባለመለየቱ አለማለየቷን ነገራት: አንድም በዕጽ ዘኢይነቅዝ አንድም በገብርኤል አድሮ ነገራት::
"ዘእንበለ ዘርዕ ኮነ ከማነ በኪነ ጥበቡ ቅዱስ: ዘተሰብአ እምኔኪ ዘእንበለ ርኩስ: ደመረ መለኮቶ:"
ከጥበብ በሚበልጥ ጥበብ ዘር ምክንያት ሳይሆን እንደኛ ሰው ሆነ ከጥበቡ በሚበልጥ ጥበቡ አለ: ዓለሙን ከፈጠረበት ሰው ሆኖ ዓለሙን ያዳነበት ትበብ ይበልጣልና: አንድም በፍጹም ጥበቡ እንደኛ ሰው ሆነ: አደፍ ጉድፍ ሳያገኝሽ ከስጋሽ ስጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆነ: መለኮቱን አዋህዶ::" ሰአሊ ለነ ቅድስት::"
መለኮቱን አዋህዶ ሰው ከሆነ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን::ታቦትን ከዚህ ይናገራሉ ሸምሸር ሸጢን ከሚባል ከማይነቅዝ እንጨት አቆልቋዩ ሁለት ክንድ ከስንዝር ቁመቱ ክንድ ከስንዝር አድርገህ ታቦትን ቅረጽ ብሎታል: በአፍአ በውስጥ በወርቅ ለብጠው: አራት ቀለበት ሁለት መሎጊያ አብጅለት ብሎታል:ምስሐልንም ሁለት ክንድ ከስንዝር ሞላልነቱ ርሁቡ ክንድ ከስንዝር ቅረጽ ብሎታል የዚህ ቁመት የለውም ሁለቱን ኪሩቤል እንደሚናተፍ አውራ ዶሮ አስመስለህ ሳላቸውዙርያውን ፈለግ አውጥተህ የማይረጋ ብጽብጽ ወርቅ አፍስስበት አለው ይህውም ምሳሌ ነው: ሁለት ክንድ ከስንዝር ከአዳም እስከ ኖህ ያለው ዘመን ነው:2256 ይሆናል : በ2256 ዘመን አርአያ ድንግል ታቦተ ኖህ ለመገኘቷ ምሳሌ ነው: ክንድ ከስንዝር ቁመት ከኖህ እስከ ሙሴ ያለው ዘመን ነው 1600 ይሆናል: በ1600 ዘመን አርአያ ድንግል ታቦተ ሙሴ ለመገኘቷ ምሳሌ ነው: ክንድ ከስንዝር ርሁብ ከሙሴ ጀምሮ እስከ እመቤታችን ያለው ዘመን ነው: 1600 ይሆናል: በ1600 ዘመን ሐመረ ኖህ እና ታቦተ ሙሴ ምሳሌዋ የሚሆኑ አማናዊት ድንግል ለመገኘቷ ምሳሌ ነው: ታቹ የንጹሃን አበው ሁለት መሎጊያ የፍቅረ ቢጽና የፍቅረ እግዚአብሔር ምሳሌ ነው: ዐራት ቀለበት በርእይ በሰሚዕ በገሢሥ በአፄንዎ በዚህ ሁሉ ንጽህት ናትና: ዳሩና ዳሩ የሃና የኢያቄም ገቢይቱ (ግበቱ) የርሷ ምሳሌ ሁለቱ ኪሩቤል የመልአከ ዑቃቢና የመልአከ መበስር ምሳለ ነው; በአመት አንድ ቀንሊቀ ካህናቱ ገብቶ በሁለቱ ኪሩቤል መካከል ድምጽ ሰምቶ ይወጣ ነበር: እርሷም በመልአከ ዑቃቢ ተጠብቃ ከመልአከ መበስር ድምጽ ሰምታ ጌታን ጸንሳ ለመገኘቷ ምሳሌ ነው: አንድም የኦሪኒና የሶፍያ ምሳሌ ነው: ባስልዮስን ከነ አትለያቸው ሳላቸው ብላዋለችና:ናንድም የዮሴፍና የሰሎሜ ምሳሌ ነው:በመከራዋ ጊዜ አልተለዩአትምና ፈለግ የልቦናዋ ምሳሌ ብጽብጽ ወርቅ የሁከት መንፈሳዊ ምሳሌ ሁከት መንፈሳዊ ከልቦና አይደለምና::
"መቅደስ ዘይኬልልዋ ኪሩቤል እለ ሥዑላን በሥዕለ እግዚአብሔር:ቃል ዘተሰባ እምኔኪ አንጽሕት ዘእንበለ ውላጤ: ኮነ ሠራዬ ሃጥያት ወደምሳሴ አበሳነ ::"
እግዚአብሔር በፈጠራቸው በኪሩቤል አምሳል ሙሴ የሳላቸው ኪሩቤል የሚጋርዱሽ መቅደስ ሙሴ አንቺ ነሽ: አንድም እግዚአብሄር በፈጠራቸው ኪሩቤል አምሳል ሰሎሞን የሳላቸው ኪሩቤል የሚጋርዱሽ መቅደስ ሰሎሞን አንቺ ነሽ: አንድም ኦ መቅደስ ዘኮነ ለሊሁ እግዚአብሄር ሊቀ ካህናት እንዲል ጌታ በማህጸን ዘደረብሽ መቅደስ አንቺ ነሽ: ሣይለወጥ ካንቺ ሰው የሆነው አካላዊ ቃል: ስለ ስጋው ስለ ነፍስ ስለ ጊዜው ስለ ዘላለሙ: ይደጋግማል በውስት በአፍአ በነፍስ በስጋ ሃጥያታችንን የሚያስተሰርይልን ሆነ::" ሰአሊ ለነ ቅድስት"
ሃጥያታችንን ከሚያስተሰርይልን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን አሜን !!!!!:: ይቆየን የእሁድን ቀጣይ ክፍል በሚቀጥለው እሁድ..........ቸር ያቆየን!

No comments:

Post a Comment